የ8ኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀን ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ተሰናድተዋል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከ ኢትዮጵያ ቡና
በድል እና በአቻ ውጤት ወደ ዕረፍት አምርተው የነበሩ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ ቀዳሚው የትኩረት ነጥባችን ይሆናል።
ከተከታታይ ድል አልባ ጉዞ በኋላ የአሰልጣኙን ቆይታ ይወስን በነበረው የመጨረሻ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን ድል በማድረግ ከተናፋቂው ሦስት ነጥብ ጋር መገናኘት የቻሉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከቆሙበት ለመቀጠል በነገው ዕለት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ይገናኛሉ።
ሊጉ ለሀገራት የማጣሪያ መርሐግብር ከመቋረጡ በፊት ድሬዳዋ ከተማን 1ለ0 በመርታት ዕፎይታን ማግኘት ችለው የነበሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በጨዋታው እንደ ቡድን ያሳዩ የነበሩትን ትጋት ነገም በድጋሚ እንደሚያስመለክቱን ይጠበቃል። ቡድኑ ዋነኛ ችግሩ ሆኖ ይታይ የነበረበትን የማጥቃት ፍላጎት ውስንነት በመጠኑም ቢሆን በድሬዳዋው ጨዋታ ላይ ማሻሻል ቢችሉም በይበልጥ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ አሁንም በቀላሉ የሚያገኟቸውን ዕድሎች ከመጠቀም አኳያ ግን ክፍተት እንደነበሩ ተመልክተናል ፤ ይሁን እንጂ ነገ የሚያስተናግዱት ኢትዮጵያ ቡናን እንደመሆኑ በተቃራኒው መከላከላቸው ላይም ዕርምትን መውሰድ የማይችሉ ከሆነ በመስመር የጨዋታ መንገድ ስል በሆነው ተጋጣሚያቸው ሊቀጡ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል።
በሲዳማ ቡና ከገጠማቸው ሽንፈት በኋላ በድል እና የአቻ ውጤት ቀጣይ ጨዋታቸውን አጠናቀው የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ይፋለማሉ።
በዕኩል ቁጥር ሁለት ድል ፣ ሁለት አቻ እና ሁለት ሽንፈትን እስከ አሁን ባደረጓቸው ጨዋታዎች ያስመዘገቡት የአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከተቀመጡበት ዘጠነኛ ደረጃ ከፍ ብሎ ለመገኘት ብርቱ ፉክክር ከተጋጣሚያቸው እንደሚጠብቃቸው ይታመናል። ሽንፈት ካስተናገዱበት የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታ በኋላ በመቐለ ላይ የ2ለ0 ድልን ሲያሳኩ በእንቅስቃሴ መሻሻሎችን አሳይተውን የነበሩት ቡናማዎች በመጨረሻው የስሑል ሽረ ጨዋታ ላይ ግን በአቀራረብ ወረድ ብለው የታዩ ሲሆን ቡድኑ የመስመር አጨዋወቱን ከፍ አድርጎ የሚገባ ከሆነ አሸናፊ የሚሆንበት ዕድል እንደሚጠብቀው መናገር ይቻላል። ቢሆንም የሚገጥሙት መከላከል ላይ በድሬዳዋው ጨዋታ ሻል ብሎ ቀርቦ የነበረውን ሀዲያ ሆሳዕናን መሆኑ ሲታሰብ ግን ጨዋታው ቀላል አይሆንላቸውም።
በሀድያ ሆሳዕና በኩል ሔኖክ አርፊጮ ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ እና አጨናቂ ፀጋዬ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆናቸው ተረጋግጧል። ቡናማዎቹ በአንጻሩ አሁንም የመስመር ተከላካያቸውን በፍቃዱ ዓለማየሁ ግልጋሎት አያገኙም።
ሁለቱም ቡድኖች በተገናኙባቸው አስር ግንኙነታቸው ዕኩል አራት አራት ጊዜ ሲሸናነፉ በሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ከተቆጠሩት ሃያ ጎሎች ደግሞ ሁለቱም ቡድኖች ዕኩል 10 ግቦችን አስቆጥረዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ መቻል
የሊጉን የመክፈቻ ጨዋታ በወላይታ ድቻ ሽንፈት ከገጠማቸው በኋላ በስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ እስከ አሁን ያልተሸነፉት እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከሊጉ መሪ መቻል ጋር የሳምንቱ ተጠባቂ መርሐግብርን ያከናውናሉ።
ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሱበት ዓመት ላይ የሚገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች አስራ ሁለት ነጥቦችን ሰብስበው በሰንጠረዡ ሦስተኛ ቦታ ላይ የተቀመጡ ሲሆን በወጥነት ጥንካሬያቸውን ለማሳደግ ነገ ከቀትር መልስ ከባዱን ጨዋታ ያደርጋሉ። ከመስመር በሚነሳው የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው በርከት ያሉ ግቦችንም ጭምር በተጋጣሚው ላይ እያስቆጠረ የዘለቀው የዘሪሁን ሸንገታው ቡድን ምንም እንኳን የአቀራረብ ለውጥ ሳይኖረው ነገም ሊቀርብ እንደሚችል ቢጠበቅም የሚገጥመው በወቅታዊ አቋሙ ወጥ በሆነ መደላድል ላይ ያለውን መቻል በመሆኑ ድክመት የሚታይበትን መከላከላቸውን ማስተካከል ካልቻሉ ግን አንዳች ነገር ሊገጥማቸው እንደሚችል ይጠበቃል።
ከሁለተኛው ሳምንት የሲዳማ ቡና ሽንፈት በኋላ በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በአቻ እና በድል ተጉዘው የሊጉ አናትን የተቆናጠጡት መቻሎች ነገም ከግስጋሴያቸው ላለመራቅ ከሌላኛው ጠንካራ ቡድን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ይፋለማሉ።
አራት ጨዋታን አሸንፈው በዕኩል ቁጥር አንድ ሽንፈት እና አቻን በማስመዝገብ ሊጉን እየመሩ የሚገኙት መቻሎች የነጥብ ልዩነቱን ለማስፋት ወደ ሜዳ የሚገቡ ይሆናል። ኳስን በበርካታ ቅብብል በመጫወት ወደ መስመር ባመዘነ እንቅስቃሴ ሲያጠቁ የሚታዩት መቻሎች በመጨረሻው የአዳማ ጨዋታቸው ላይ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር አሸንፈው ቢወጡም በተለይም በመጀመሪያ አጋማሽ የነበረባቸውን መጠነኛ የእንቅስቃሴ መቀዛቀዝ በነገው ዕለት ማስተካከል የግድ ይላቸዋል። በአንፃሩ ቡድኑ የመስመር አጨዋወቱን ከፍ አድርጎ የሚቀርብ ከሆነ የኤሌክትሪክን የኋላ መስመር ጫና ውስጥ እንደሚከተው ይታመናል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከጉዳትም ሆነ ቅጣት ነፃ የሆነውን ስብስብ በመያዝ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሃያ ስምንት ጊዜ ተገናኝተው ኤሌክትሪክ አሥር በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መቻል አምስት አሸንፎ በአሥራ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። መቻል 31 ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ ደግሞ 42 ግቦች አሉት።