ሪፖርት | ሀድያ ሆሳዕና ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን አሳክተዋል

ነብሮቹ በተመስገን ብርሀኑ የሁለተኛ አጋማሽ ብቸና ግብ ቡናማዎቹን 1ለ0 በመርታት ሁለተኛውን ተከታታይ ድላቸውን ተቀዳጅተዋል።

ሀድያ ሆሳዕና ከሊጉ መቋረጥ በፊት ድሬዳዋ ላይ ድል ከተቀዳጀው ቡድን ውስጥ ደስታ ዋሚሾን በእዮብ ዓለማየሁ ፣ ፀጋአብ ግዛውን በተመስገን ብርሀኑ ሲተኩ ከስሑል ሽረ ጋር ነጥብ ተጋርተው የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ዋሳዋ ጂኦፌሪን በይታገሱ ታሪኩ በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል።

በፌድራል ዋና ዳኛ አባይነህ ሙላት እየተመራ በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናዎች በእንቅስቃሴ የበላይ በመሆን ብልጫውን ቢይዙም የጠሩ የግብ አጋጣሚዎች ማግኘቱ ላይ ግን ውስንነቶች ነበረባቸው።

በአንፃሩ ተጋጣሚያቸው በኳስ ምስረታ ከራሳቸው ሜዳ ለመውጣት ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት የሚፈጥሯቸውን ስህተቶች በመልሶ ማጥቃት ነብሮቹ ለመጫወት አልመው ቢንቀሳቀሱም ጨዋታው በአመዛኙ ሐይል የተቀላቀለበት መሆኑ የግብ አጋጣሚዎች ተፈጥረው እንዳንመለከት ዳርጎናል።

ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እየተስተዋለ በቀጠለው ጨዋታ 14ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ሽፈራው በኢትዮጵያ ቡና በኩል ሙከራን አድርጎ በግቡ ቋሚ ብረት ስር ታካ የወጣችዋ ጥረት ቀዳሚዋ ሙከራ ነበረች።

በይበልጥ ከራስ ሜዳ በነፃነት በቅብብል በመውጣት ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ቡናማዎች በተደጋጋሚ ሲደርሱ ይስተዋል እንጂ በቁጥር በዝተው በመከላከሉ ጥብቅ የነበሩትን የሀድያ ሆሳዕናን የኋላ ክፍል ማስከፈት ላይ እጅጉን ከብዷቸው ማየት ችለናል። በድግግሞሽ መቆራረጦች በበዙበት የአጋማሹ የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች ከመከላከል በተጨማሪ በመልሶ ማጥቃት በመጠኑ ለመንቀሳቀስ የዳዱት ነብሮቹ ሠመረ ለብሩክ ለማቀበል ብሎ በሚያስቆጭ መልኩ ካመከናት ዕድል ውጪ ብዙም በሙከራዎች መድመቅ የተሳነው አጋማሽ ያለ ጎል ተገባዷል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ኢትዮጵያ ቡናዎች በረጃጅም ኳስ ለመጫወት ያለመ የሚመስል የተጫዋች ቅያሪን ሲያደርጉ ዳዊት ሽፈራውን በሲዲ ማታላ ለውጠው ሲመለሱ ከመጀመሪያው በብዙ መልኩ መቀዛቀዞች የታዩበት ሁለተኛው አጋማሽ የማጥቃት ቁጥራቸውን ከፍ ያደረጉት ሀድያ ሆሳዕናዎች ቢሆኑም ሙከራን በማድረጉ ግን ቡናዎች ቀዳሚ ሆነዋል።

62ኛው ደቂቃ ይታገሱ ታሪኩ ከቀኝ ያሻማውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ያገኘው ዲቫይን ዋቹኩዋ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት አምልጣዋለች። መልሶ ማጥቃታቸውን በይበልጥ እያጎለበቱ የተጓዙት ነብሮቹ 70ኛው ደቂቃ ከድር ኩሊባሊ በረጅሙ የጣለውን ኳስ ኦካይ ጁል በግንባር ሲጨርፋት ከጀርባ የነበረው ተመስገን ብርሀኑ በጥሩ አጨራረስ ወደ ጎልነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል።


ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ስል በሆነ እንቅስቃሴ የቀጠሉት ሀድያ ሆሳዕናዎች በተመስገን ሌላ ያለቀለት ዕድልን አግኝተው በግብ ዘቡ ዳላንድ ኢብራሂም ስትመለስበት ዳግም የተመለሰችውን ኳስ ያገኘው መለሠ ሚሻሞ ሞክሯት በተከላካዮች ተደርባ ወጥታለች።

ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመግባት እንቅስቃሴ ቢያደርጉም የሀድያን የኋላ አጥር ሰብሮ መግባት ግን የተሳናቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጨረሻም 1ለ0 በሆነ ውጤት መረታት ችለዋል።