በሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል ለውጦች ሊያመጡ የሚችሉ እና ጠንካራ ፉክክር ይደረግባቸዋል ተብለው የሚገመቱ የ9ኛው ሳምንት መክፈቻ ጨዋታዎች አስመልተን ያዘጋጀናቸው መረጃዎች እነሆ!
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ኢትዮጵያ መድን
ሻምፕዮኖቹ ደረጃቸውን ለማሻሻል ኢትዮጵያ መድን ደግሞ ወደ ሰንጠረዡ አናት ይበልጥ ለመጠጋት የሚያደርጉት ፍልምያ የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ነው።
ዓምና ሊጉን በበላይነት ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከተቀዛቀዘው የዘንድሮ አጀማመር ተላቆ ወደ ሚታወቅበት ውጤታማነት ለመምጣት የሚንደረደርበትን አዎንታዊ ውጤት ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይገመታል።
ከሦስት ተከታታይ ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ወልዋሎን አሸንፎ ወደ ድል መንገድ የተመለሰው ቡድኑ በሊጉ አምስት ጨዋታዎችን አከናውኖ ሰባት ነጥቦች ሰብስቧል። በተለያዩ ምክንያቶች አነስተኛ የጨዋታ መጠን ማድረግ ቢችሉም በርከት ያሉ ግቦች ያስተናገዱት ንግድ ባንኮች በጨዋታ በአማካይ 1.4 ግቦች ማስተናገድ ችለዋል። በነገው ጨዋታም በመጨረሻዎቹ ሦስት መርሃግብሮች ሰባት ግቦችን ተጋጣሚ መረብ ላይ ያዘነቡትን ኢትዮጵያ መድኖች እንደመግጠማቸው በተሻለ የመከላከል አቅም ወደ መቅረብ ግድ ይላቸዋል።
አሰልጣኝ በፀሎት የመከላከል አደረጃጀታቸው ላይ ለውጦች ማድረግ ቀዳሚ ስራቸው ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም ከሁለተኛው ሳምንት በኋላ በውስን መልኩ የተዳከመው እና በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው የፊት መስመራቸው ወደ ቀደመ ውጤታማ ብቃቱ የመመለስ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።
ተከታታይ ሦስት ድሎች በማስመዝገብ መሪዎቹን እግር በእግር መከታተላቸውን የቀጠሉት ኢትዮጵያ መድኖች አስራ ሦስት ነጥቦች በመሰብሰብ ከመሪው በሁለት ነጥብ ዝቅ ብለው 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
በስድስት መርሃግብሮች መረቡን ያላስደፈረው እንዲሁም በሰባት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደው የማይደፈረው የመከላከል አደረጃጀት የኢትዮጵያ መድን ዋነኛ ጠንካራ ጎን ነው።
አምና ሊጉን በጨረሱበት ጥንካሬ ለመቀጠል እና የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ድል ለማስመዝገብ አራት ሳምንታት የፈጀባቸው መድኖች በመጀመርያዎቹ መርሃግብሮች የነበራቸው የፊት መስመር ድክመት ከውጤት ቢያራርቃቸውን በሂደት ወደ ጥሩ ብቃት በመምጣት በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ድል አድርገዋል።
ቡድኑ በመከላከሉ ላይ ባስመዘገባቸው አስደናቂ ቁጥሮች መነሻነት የኋላ ክፍሉ የቡድኑ ጥንካሬ የትኩረት ማዕከል ቢሆንም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስመዘገበ የፊት መስመር ጥምረቱ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ የውህደት ደረጃው ከፍ ያደረገው የአማካይ ክፍሉም ሌሎች የቡድኑ ጠንካራ ጎኖች ናቸው።
ጨዋታው ለወትሮም ቢሆን ለኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቅድሚያ የሚሰጠው አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ
እና ለዓመታት ከሚታወቁበት ቀጥተኛ አጨዋወት ፈቀቅ በማለት በተወሰነ መልኩ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ የሚጥር ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ መካከል የሚደረግ እንደመሆኑ የአማካይ ክፍሉ የበላይነት ከጨዋታው ውጤት ጋር በቀጥታ የሚያያዝ እንደሚሆን ይገመታል።
በኢትዮጵያ መድን በኩል በመጨረሻው መርሃግብር በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጡት ተከላካዮቹ ዋንጫ ቱት እና ሚልዮን ሰለሞን በቅጣት አይሰለፉም። በንግድ ባንክ በኩል ደግሞ ሱለይማን ሀሚድ በጉዳት አይኖርም። ኪቲካ ጀማ እና ባሲሩ ዑመር ከጉዳት ሲያገግሙ ኤፍሬም ታምራት በቅጣት አይሰለፍም።
ክለቦቹ በታሪካቸው 22 ጊዜ የተገናኙት ሲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስር፣ ኢትዮጵያ መድን ደግሞ ሦስት ጊዜ ስያሸንፉ ዘጠኝ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ንግድ ባንክ 36፣ መድን ደግሞ 22 ግቦችን አስቆጥረዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ድሬዳዋ ከተማ
ከመሪዎቹ በታች ባለው የሰንጠረዡ ክፍል ለተቀመጡት ሁለቱ ቡድኖች የነገው ጨዋታ አሸናፊውን ወደ መሪዎቹ የማስጠጋት አጋጣሚን ይዞ የሚመጣ እንደመሆኑ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይታመናል።
ለሰባት ተከታታይ ሳምንታት ሽንፈት አልባ ጉዞ በማድረግ አስራ ሦስት ነጥቦች የሰበሰቡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከብዙዎች ግምት የራቀ አስደናቂ ጉዞ በማድረግ ከመሪው በአንድ ነጥብ ዝቅ ብለው 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ቡድናቸው ከኢትዮጵያ መድን ጋር አቻ ከተለያየበት የ3ኛ ሳምንት ጨዋታ በኋላ በሶከር ኢትዮጵያ የድህረ ጨዋታ አስተያየት ላይ ቡድናቸው ለመከላከሉ ልዩ ትኩረት የሰጠ አቀራረብ እንደሚኖረው የገለፁት አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በቅርብ ሳምንታት የመከላከል አደረጃጀታቸው ጥንካሬ በሚፈልጉት መንገድ የሄደላቸው አይመስልም። ቡድኑ በተከታታይ አራት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር ከወጣባቸው መርሃግብሮች በኋላ ባከናወናቸው ሦስት ጨዋታዎች አራት ግቦች አስተናግዷል። ይህንን ተከትሎ በነገው ዕለት የመከላከል አደረጃጀቱን ጥንካሬ መመለስ የአሰልጣኙ ቀዳሚ የቤት ስራ ይሆናል ተብሎ ይገመታል።
ኤሌክትሪክ በሊጉ የመጀመርያ ሳምንታት ከነበረበት የመከላከል ጥንካሬ በአንፃራዊነት ውስን ድክመቶች ቢስተዋልበትም የፊት መስመሩ ውጤታማነት ከፍ ማለቱ ግን በቅርብ ሳምንታት ያስቆጠራቸው ግቦች መጠን ምስክር ናቸው። በነገው ጨዋታም ከተጋጣሚያቸው የጨዋታ ዕቅድ መነሻነት ውጤታማ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶች ያገኛሉ ተብሎ ይገመታል።
ከአራት ጨዋታዎች መልስ ሀዋሳ ከተማ ላይ መጠነኛ እፎይታ የሰጣቸውን ድል ያስመዘገቡት ብርቱካናማዎቹ አሁንም በነጥብ ረገድ ከመሪዎች ተርታ ባይርቁም በውጤትም ይሁን በብቃት ደረጃ ውስን የወጥነት ችግር ይስተዋልባቸዋል።
ሊጉን በጀመሩበት ጥሩ ብቃት እንዲሁም
ቡድኑ ካለው የስብስብ ጥራት መነሻነት ለዋንጫ ተፎካካሪነት ቢታጩም በመሀል የውጤት ውጣ ውረድ ውስጥ የገቡት ብርቱካናማዎቹ ከሳምንታት ጥበቃ በኋላ ያገኙትን ወሳኝ ድል ለማስቀጠል ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል።
ኳስን በመቆጣጠር ረገድ የማይታሙት ድሬዳዋ ከተማዎች በነገው ጨዋታም ተመሳሳይ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም ለመልሶ ማጥቃት እና ፈጣን ሽግግሮች ተጋላጭ የሆነው የመከላከል አደረጃጀታቸው ላይ ማስተካከያዎች ማድረግ ግድ ይላቸዋል። ቡድኑ በሊጉ ውጤታማ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ካላቸው ቡድኖች አንዱ ከሆነው ሀዋሳ ከተማ ጋር ባከናወነው ጨዋታ ከስድስት መርሃግብሮች ጥበቃ በኋላ መረቡን ሳያስደፍር መውጣቱ እንደ አወንታ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም የመልሶ ማጥቃት አጨዋወቱ ጥራት ከፍ በማድረግ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ላስቆጠረው የኤሌክትሪክ መልሶ ማጥቃት የሚመጥን ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል።
ከምንም በላይ የመከላከል አደረጃጀታቸው ጥንካሬ
ወሳኝ ይሆናል ተብሎ ቢገመትም ቡድኑ ድል ባስመዘገበባቸው ጨዋታዎች ላይ ትልቅ ሚና የነበረው የመስመር አጨዋወት ውጤታማነትም የነገው ጨዋታ ልዩነት ፈጣሪ ይሆናል ተብሎ ይታመናል።
በኤሌክትሪክ በኩል አበባየሁ ዩሐንስ፣ አባይነህ ፌኖ እና በፍቃዱ አስረሳኸኝ አገግመው ለነገው ጨዋታ ሲደርሱ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በቅጣት ከነገው ጨዋታው ውጭ ነው፤ ከዚህ በተጨማሪ የሀብታሙ ሸዋለም መሰለፍ አጠራጣሪ ነው። ድሬዳዋ ከተማዎች በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ16 ጊዜያት ተገናኝተው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በስድስት፤ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በአራት አጋጣሚዎች ሲያሸንፉ ቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ የተጠናቀቁ ነበሩ። ኤሌክትሪክ 20 ድሬዳዋ ደግሞ 14 ግቦችን ማስቆጠርም ችለዋል።