ሪፖርት | ንግድ ባንክ እና መድን አቻ ተለያይተዋል

ሁለቱን የመዲናይቱ ክለቦች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮጵያ መድንን ያገናኘው ጨዋታ 1ለ1 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ባለፈው ሳምንት አራፊ ከመሆናቸው በፊት ወልዋሎን ያሸነፈው ቡድናቸውን ለዛሬው ጨዋታ ይዘው ሲቀርቡ አዳማ ከተማን ድል ያደረጉት ኢትዮጵያ መድኖች በበኩላቸው በቅጣት እና ጉዳት ባጧቸው ሚሊዮን ሠለሞን ፣ ዋንጫ ቱት እና አቡበከር ሳኒ ምትክ አዲስ ተስፋዬ ፣ በረከት ካሌብ እና መሐመድ አበራን በቋሚ አሰላለፍ በማካተት ቀርበዋል።

 

10 ሰዓት ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው መሪነት በጀመረው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኖች ለ15 ያህል ደቂቃዎች ባደረጉት ጥሩ አጀማመር ጎልን ያስቆጠሩበት ነበር። በ12ኛው ደቂቃ ሀይደር ሸረፋ ከንግድ ባንኩ አማካይ ባሲሩ ዑመር የነጠቀውን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግራ የጣለውን ኳስ ረመዳን የሱፍ ከአብዱልከሪም መሐመድ ጋር ታግሎ ይዞ ወደ ውስጥ በመግባት ኳሷን ወጋ አድርጎ መረብ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ተመጣጣኝ የጨዋታ አቀራረቦችን ነገር ግን በአመዛኙ የንግድ ባንክ የእንቅስቃሴ የበላይነትን ያስመለከተን ቀጣዩ ደቂቃ ወደ መስመር በረጅሙ በሚደርሱ ኳሶች በጥልቀት ለመጫወት ጥረት ያደረጉበትን ሒደት ብንመለከትም ቡድኑ ሦስተኛው ሜዳ ላይ የነበረው ስልነት ግን በእጅጉ የተዳከመ ነበር። በሌላ በኩል መሐል ሜዳ ላይ ጥሩ ኳሶችን ለማደራጀት ጥረት ሲያደርግ የነበረውን አማካዩ ፉዓድ ፈረጃን 32ኛው ደቂቃ ላይ ከበድ ባለ ጉዳት በብሩክ እንዳለ ለመተካት ከተገደዱ በኋላ የቡድኑ የፈጠራ አቅም ማነስ ብቻም ሳይሆን ዕድሎችን በቀላሉ ወደ ወደ ጎልነት ለመቀየር የነበራቸው ተሳትፎ ደካማ ነበር።

ጥንቃቄ ላይ ባመዛኙ ትኩረት ሰጥተው የሚያገኟቸውን መጠነኛ ኳሶች በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ያደርጉ የነበሩት መድኖች ተሳክቶላቸው አጋማሹን 1ለ0 እየመሩ አጠናቀዋል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ የአንድ ፣ አንድ ተጫዋች ቅያሪን በማድረግ ነበር ወደ ሜዳ የገቡት ፣ ፈጠን ያሉ ሽግግሮች በይበልጥ በተስተዋለበት አጋማሽ ንግድ ባንኮች በመስመር በኩል ባደረጉት ጥልቅ አጨዋወት 52ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ጎልነት አግኝተዋል። ኪቲካ ጀማ ከግራ ኳስ ይዞ ሲገባ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ በተጫዋቹ ላይ በሳጥን ውስጥ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አዲስ ግደይ ከመረብ አሳርፎ ጨዋታው ወደ 1ለ1 ተሸጋግሯል።

በእንቅስቃሴ ዝግ ከማለታቸው ባለፈ የኃይል አጨዋወትን የሚጠቀሙት መድኖች በተጋጣሚያቸው የሽግግር ጨዋታ ተጋላጭነታቸው እየጨመረ በተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲያስተናግዱ ተመልክተናል። 68ኛው ደቂቃ ሲሞን ከቀኝ ወደ ውስጥ የላከውን ኳስ ኪቲካ የግቡ ሁለት ሜትር ላይ ሆኖ ሲመታ የግብ ዘቡ አቡበከር ኑራ በአስደናቂ መልኩ ያወጣበት እና ከሁለት ደቂቃ መልስ ደግሞ ሲሞን ፒተር በአንድ ለአንድ ግንኙነት በድጋሚ በአቡበከር የመከነበት አጋጣሚም እጅግ የንግድ ባንክን የበላይነት ያመላከቱ ያለቀላቸው ሙከራዎች ነበሩ። አሸንፎ ለመውጣት ማጥቃቱ ላይ ትኩረት አድርገው ንግድ ባንኮች ጫናዎችን ለማሳደር ብልጫውን ይዘው የነበረ ቢሆንም የመድኖችን የኋላ ክፍል ማስከፈቱ ተስኗቸው በመጨረሻም ጨዋታው 1ለ1 ሊቋጭ ችሏል።