ጥሩ ፉክክር እና በርከት ያሉ ሙከራዎች የተደረጉበት ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመቻል ጋር አቻ ከተለያየው ቋሚ አሰላለፍ ሀብታሙ ሽዋለም እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስን አስወጥተው በቢንያም በቀለ እና አሸናፊ ጥሩነህ ቀይረው ሲገቡ ድሬዳዋ ከተማዎችም ሀዋሳ ላይ ድል ካደረገው ቋሚ ሄኖክ ሐሰን እና ሱራፌል ጌታቸውን በአቤል አሰበ እና ሙኸዲን ሙሳ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ምሽት 1 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ዓባይነህ ሙላት መሪነት ተጀምሮ ጠንካራ ፉክክር እና በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች የታዩበት የመጀመርያው አጋማሽ ተቀራራቢ የሚባል የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ቢታይበትም ብርቱካናማዎቹ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች በማድረግ ብልጫ ነበራቸው። ድሬዳዋ ከተማዎች ካደረጓቸው ሙከራዎች ውስጥም ሙኸዲን ሙሳ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ አክርሮ መቷት ግብ ጠባቂው በሚያስደንቅ ብቃት ያዳናት እንዲሁም መሐመድኑር ናስር እና ቻርለስ ሙሴጌ በተመሳሳይ በረዥሙ የተላከላቸውን ኳስ ተጠቅመው ከግቡ የቅርብ ርቀት ላይ ሆነው ሞክሯቸው በግብ ጠባቂው የመከኑ ኳሶች ድሬዳዋ ከተማን ቀዳሚ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ።
ለግብ የቀረበ ሙከራ ለማድረግ ዘለግ ያሉ ደቂቃዎች ለመጠበቅ የተገደዱት ኤሌክትሪኮች በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ፍቃዱ ዓለሙ ከመስመር የተሻገረችውን ኳስ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ መቷት አብዩ ካሳዬ በጥሩ ብቃት ያዳናት ኳስም ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ወርቃማ ዕድል ነበረች። በአጋማሹ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ግብ ጠባዊ ኢድሪሱ አብዱላሂ ያለቀላቸውን ኳሶች በማዳን ጥሩ ብቃቱን ዐሳይቷል።
እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ሁለተኛው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች ሙሉ ብልጫ ወስደው በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች ያደረጉበት ነበር። ብርቱካናማዎቹ ከአጋማሹ የመጀመርያ ደቂቃዎች የተሻለ ብልጫ ቢወስዱም የተሻሉ የግብ ሙከራዎች ማድረግ የቻሉት ግን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ነበሩ። በተለይም ከቀኝ መስመር ተሻግራ ከግብ ጠባቂው ፊት ለፊት የነበረው ተመስገን ደረስ በማይታመን ሁኔታ ወደ ግብነት ያልቀየራት እና በተመሳሳይ ከመስመር ተሻግራ መሐመድኑር ናስር ጨርፏት ከግቡ አፋፍ የነበረው ተመስገን ደረስ መቷት ተከላካዮች እንደምንም ተደርበው ያወጧት ኳስ ድሬዳዋ ከተማን አሸናፊ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ።
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ግሩም የመከላከል አደረጃጀት እና የድሬዳዋ ከተማ የማያቋርጥ ጥቃት የታየበት የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ቢያስመለክተንም ግብ ሳይስተናገድበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።