ሪፖርት| ጦሩ መሪነቱን ያጠናከረበት ድል አስመዝግቧል


ሽመልስ በቀለ ሁለት ግቦችን ባስቆጠረበት ጨዋታ መቻል አርባ ምንጭ ከተማን ረቷል

አዞዎቹ ወልዋሎን ካሸነፈው ስብስብ አንዱዓለም አስናቀ በይሁን እንደሻው ተክተው ሲገቡ መቻሎች በበኩላቸው ከኤሌክትሪክ ጋር አቻ ከተለያየው ቋሚ አሰላለፍ ዳዊት ማሞ፣ አብዱልከሪም ወርቁ እና አቤል ነጋሽ በዓለምብርሀን ይግዛው፣ ሽመልስ በቀለ እና ዳንኤል ዳርጌ ተክተው ገብተዋል።

ጠንካራ ፉክክር በታየበት የመጀመርያው አጋማሽ መቻሎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ይዘው ለመጫወት ሲሞክሩ አርባ ምንጮች በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል።

ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ቢታይበትም ጥቂት ሙከራዎች የተስተናገዱበት ነበር። ሆኖም ግሩም ሀጎስ አሻምቷት ሳጥን ውስጥ የነበረው ምንይሉ ወንድሙ ወደ ግብ መቷት ፋሪስ አለዊ በድንቅ ብቃት ባወጣት ኳስ ጥቃታቸው የጀመሩት መቻሎች ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ ነበሩ።

በሀያ ስምንተኛው ደቂቃም ጥረታቸው ሰምሮ በሽመልስ በቀለ አማካኝነት መሪ መሆን ችለዋል ፤ አማካዩ ግሩም ሀጎስ ያሻገራትን ኳስ ከተቆጣጠረ በኋላ ተከላካዮችን አልፎ ከፍ አድርጎ በመምታት ነበር ያስቆጠረው።

መቻሎች ከግቧ በኋላም በረከት ደስታ አክርሮ መቷት ግብ ጠባቂው ባዳናት ሙከራ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም አርባምንጭ ከተማዎች ግን በፍቅር ግዛው ከአሕመድ ሑሴን የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ካደረጋት ለግብ የቀረበች ሙከራ ውጭ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም።

ከመጀመርያው አጋማሽ ተመሳሳይ መልክ የነበረው ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ነበር። እንደ መጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው መቻሎች በአጋማሹ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳያደርጉ ከቆዩ በኋላ በሀምሳ ስድስተኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል ፤ ምንይሉ ወንድሙ በረጅሙ አሻግሯት ሽመልስ በቀለ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያስቆጠራት ግብም የጦሩ መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችላለች።

እንዳልካቸው መስፍን በሁለት አጋጣሚዎች ባደረጋቸው ሙከራዎች እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ያደረጉት አዞዎቹም በሰባ ስድስተኛው ደቂቃ ጥረታቸው ሰምሮ በአሕመድ ሑሴን አማካኝነት ግብ አስቆጥረው የግብ ልዩነቱን ማጥበብ ችለዋል፤ አጥቂው ከቀኝ መስመር የተሻገረችውን ኳስ በግንባር በመግጨት ነበር ያስቆጠራት።

ሁለቱም ቡድኖች ባደረጓቸው ቅያሪዎች የቀጠለው ጨዋታው በሰማንያኛው ደቂቃ በአርባ ምንጭ ሳጥን ውስጥ በተሰራው ጥፋት መቻሎች የፍፁም ቅጣት ምት ማግኘት ቢችሉም ምንይሉ ወንድሙ ኳሷ ከግቡ በላይ በመሰደድ ኳስና መረብ ሳያገናኝ ቁርቷል።


ሆኖም በሰማንያ አምስተኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው አብዱ ሙታላቡ በግሩም ሁኔታ የሰነጠቃት ኳስ በተመሳሳይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አብዱልከሪም ወርቁ ከመረብ ጋር አዋህዷት የቡድኑን መሪነት በማሳደግ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታ በጦሩ የበላይነት እንዲደመደም አስችሏል።