የዘጠነኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎችን የተመለከቱ ዝርዝር ጥንቅሮችን በተከታዩ ዘገባችን ይዘንላችሁ ቀርበናል።
ወላይታ ድቻ ከ ሀዋሳ ከተማ
በሊጉ በሁለት የተለያየ የውጤት ጎዳና ላይ የሚገኙ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሊጉ ጠንካራ አቋምን እያሳዩ ካሉ ቡድኖች መካከል አንዱ በመሆን የደረጃ ሰንጠረዡ የላይኞቹ ስፍራ ላይ መቀመጥ የቻሉት ወላይታ ድቻዎች ከድል ጋር ከተራራቁ ሦስት ጨዋታዎች ካለፋቸው ሀዋሳ ከተማዎች ጋር ይገናኛሉ።
ከስምንት ሳምንታት በአራቱ ድልን በተመሳሳይ ሁለት ቁጥሮች ደግሞ የሽንፈት እና የአቻላቻ ውጤቶችን በመያዝ ከመሪው መቻል በሦስት ነጥቦች አንሰው አስራ አራት ነጥቦችን ይዘው የሚገኙት የጦና ንቦቹ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ከገጠማቸው የአቻ ውጤቶች የሚያላቅቃቸውን ድል ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ። በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት አያስተናግዱ እንጂ ከሽግግር አጨዋወታቸው እና በሒደት ከገነቡት ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት በሁለቱ ያለፉትን መርሐግብሮች መቀዛቀዝ የታየበት ቡድኑ መጠነኛ ማሻሻያን የሚያደርግ ከሆነ ወሳኝ ድልን ነገ ማሳካቱ አይቀርም ነገር ግን ቡድኑ በውጤት ቀውስ ውስጥ ያለውን ሀዋሳን እንደመግጠሙ ሊገጥመው የሚችለው ፈተና ቀላል የሚባል አይሆንም።
በአራተኛው ሳምንት ሀድያ ሆሳዕናን 2ለ1 ካሸነፉ በኋላ በነበሯቸው ቀጣይ ጨዋታዎች ሦስት ነጥብን ማግኘት የተሳናቸው ሀዋሳ ከተማዎች ከሦስት ሽንፈቶች መልስ የድል መንገድ ውስጥ ለመገኘት ሌላኛውን ትልቅ ፈተና በነገው ዕለት መጋፈጥ ግድ ይላቸዋል።
በሁለት ድል ፣ በአራት ሽንፈቶች እና በአንድ የአቻ ውጤቶች ግርጌ ላይ ከተቀመጠው ወልዋሎ በአንድ ደረጃ ብቻ ከፍ ብለው አስራ ሰባተኛ ላይ የተቀመጡት ሀዋሳ ከተማዎች በብዙ መሻሻል የሚኖርባቸው ይሆናል። ሊጉን ሲጀምሩ ፈጣን ከሆነው የሽግግር አቀራረብ በተጨማሪ በመከላከሉም ጠጣር አደረጃጀትን ቢያሳዩንም በሒደት በብዙ ረገድ ተዳክመዋል ፣ ቡድኑ ባለፈው ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ በአቻ ውጤት ጨዋታውን አጠናቀቀ ተብሎ ሲጠበቅ በመጨረሻ ደቂቃ በተከላካዮች ዝንጉነት ግብ ማስተናገዳቸው ማሳያ የሚሆን ሲሆን ይህንን መድፈን የማይችሉ ከሆነ ግን ፈጣን ሽግግሮችን በሚያዘወትረው ወላይታ ድቻ አንዳች ነገር ሊያስተናግዱ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል።
ወላይታ ድቻ ከጉዳትም ሆነ ቅጣት ነፃ የሆነውን ስብስብ በመያዝ ለጨዋታው ሲቀርቡ የሀዋሳ ከተማን የቡድን ዜና ለማካተት ያደረግነው ጥረት ግን አልተሳካም።
ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ እስከ አሁን ለ20 ጊዜያት ያህል የተገናኙ ሲሆን በተመሳሳይ ቁጥር ሰባት ሰባት ጊዜ ተሸናንፈዋል። በስድስት አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ሲለያዩ ወላይታ ድቻ 21 ፤ ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 24 ግቦችን በግንኙነታቸው አስቆጥረዋል።
ስሑል ሽረ ከ ሀድያ ሆሳዕና
የሳምንቱ የመጨረሻ የሆነው መርሐግብር ምሽት ላይ ይደረጋል።
ወደ ሊጉ በተመለሱበት የመጀመሪያ ጨዋታ አዳማ ከተማን ካሸነፉ በኋላ ባደረጓቸው ስድስት መርሐግብሮች በጠቅላላ ሦስት ነጥብን ደግመው ያላገኙት ስሑል ሽረዎች ነገ የዓመቱ ሁለተኛ ድልን ለማግኘት በወቅታዊ አቋማቸው ጥሩ የሚባሉት ነብሮቹን ይገጥማሉ።
ማግኘት ከሚገባው አስራ ስምንት ነጥቦች አራት ነጥቦችን ብቻ በማሳካት በድምሩ ሰባት ነጥቦችን ይዞ አስራ ስድስተኛ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ በመከላከል አቀራረብ ለተጋጣሚ ቡድኖች ፈታኝ ሆኖ ቢታይም የግብ ዕድሎችን መፍጠር ላይ ግን በእጅጉ መዳከሞችን በድግግሞሽ ያስመለከተን ሲሆን ይህንንም ችግር አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ባለፈው ሳምንት በባህር ዳር ከተማ 2ለ0 በተረቱበት ወቅት የግብ ዕድሎችን ወደ ጎልነት ከመለወጥ አንፃር ድክመት እንዳለባቸው ለዝግጅት ክፍላችን የተናገሩ ሲሆን ይህንን የአጨራረስ ውስንነትም በነገው ጨዋታ ላይ ቀርፎ መገኘት ቀዳሚ ጉዳያቸው እንደሚሆን ይታመናል።
ከድል አልባ ጉዞዎች መልስ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን በተመሳሳይ የ1ለ0 ውጤቶች በማሸነፍ ዕፎይታን ያገኙት ሀድያ ሆሳዕናዎች ሰሞነኛውን የድል ፌሽታቸውን ወደ ሦስት ከፍ ለማድረግ ስሑል ሽረን ነገ በሳምንቱ የማሳረጊያ ቀን ይገጥማሉ።
ሦስት ሽንፈት ፣ ሦስት ድል እና አንድ የአቻ ውጤትን በመያዝ በሰንጠረዡ ወገብ ላይ ተቀምጦ የሚገኘው የአሰልጣኝ ግርማ ታደሠው ስብስብ በጥብቅ የመስመር ማጥቃት አጨዋወት እያሳዩ የሚገኙትን በቡድን የመንቀሳቀስ ህብረት ነገም በድጋሚ እንደሚያስመለክቱን የሚጠበቅ ቢሆንም አሁንም በመስመር መከላከል ተጋላጭ ሲሆኑ በተወሰነ መልኩ መመልከት የቻልን ሲሆን የሚገጥሙት በአንፃሩ በመስመር ስል የሆነውን ስሑል ሽረን በመሆኑ በይበልጥ ወደ ጥንቃቄው እንደሚያመዝኑ ይጠበቃል።
በስሑል ሽረ በኩል ኤልያስ አህመድ አሁንም በግል ጉዳይ ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን ጉዳት ላይ የነበሩት አሌክስ ኪታታ ፣ ክፍሎም ገብረሕይወት እና ሱለይማን መሐመድ ልምምድ ቢጀምሩም የመሰለፋቸው ጉዳይ ግን አጠራጣሪ ነው። በሀድያ ሆሳዕና በኩል ሔኖክ አርፊጮ ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ እና በረከት ወንድሙ እንዲሁም ለረጅም ወራት ጉዳት ላይ የነበረው ጫላ ተሺታ ወደ ልምምድ ቢመለሱም ለነገው ጨዋታ ግን የማይደርሱ ይሆናል።
ሁለቱ ቡድኖች በተሰረዘው እና ባዶ ለባዶ ከተጠናቀቀው የ2012 ውድድር ዓመት ጨዋታ ውጭ ተገናኝተው አያውቁም።