ሪፖርት | የጦና ንቦቹ እና ኃይቆቹን ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ

በንትርኮች ታጅቦ የተካሄደው ጨዋታ በአቻ ውጤት ፍጻሜውን አግኝቷል።

የጦና ንቦች ከፋሲል ከነማ ጋር አቻ ከተለያየው ቋሚ አሰላለፍ ፍፁም ግርማ አሳርፈው በተስፋዬ መላኩ ተክተው ሲገቡ ኃይቆቹ በበኩላቸው በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈት ካስተናገደው ቋሚ ታፈሰ ሰለሞን፣ አማኑኤል ጎበና እና ተባረክ ሔፋሞን አስወጥተው በወንድማገኝ ኃይሉ፣ ማይክል ኦቱሉ እና ዮሴፍ ታረቀኝ ተክተው ገብተዋል።

ብዙም ማራኪ ያልነበረው እና በአወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎቹ እና እነሱን ተከትለው ተፈጠሩ እሰጣ ገባዎች ታጅቦ የተካሄደው የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታዩበት ነበር። በማጥቃቱ ረገድ በአንጻራዊነት የተሻሉ የነበሩት ኃይቆቹ በመጀመሪያዎቹ እንዲሁም በአጋማሹ መገባደጃ ደቂቃዎች ካመከኗቸው ሁለት ጥሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ውጭ በዓሊ ሱሌይማን አማካኝነት ዒላማዋን የጠበቀበች ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። በአጋማሹ መሳይ ሰለሞን ከርቀት ባደረጋት ሙከራ የተጋጣሚን ግብ መፈተሽ የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች የተጠቀሰችው ሙከራ እንዲሁም አብነት ደምሴ በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ካደረጋት ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም።

የሀዋሳ ከተማ ብልጫ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በእንቅስቃሴም ይሁን በሙከራዎች ረገድ ከመጀመሪያው የጨዋታው ምዕራፍ የተሻለ ነበር። በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው ዮሴፍ ታረቀኝ በተሰለፈበት ጥሩ የማጥቃት አቅም የነበራቸው ኃይቆቹ በዓሊ ሱሌይማን እና ዓብዱልበሲጥ ከማል ሁለት ያለቀላቸው ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ኳስ እና መረብ ማገናኘት አልቻሉም። በተለይም አጥቂው ከአማካይ ክፍል በጥሩ መንገድ የተሰነጠቀችለትን ኳስ አዙሮ መቷት ግብ ጠባቂው ያዳናት ኳስ ቡድኑም መሪ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።

ኃይቆቹ ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም በ80ኛው ደቂቃ ግን የጦና ንቦቹ በብሥራት በቀለ አማካኝነት ግብ በማስቆጠር ጨዋታውን መምራት ችለዋል። የጦና ንቦቹ ቴዎድሮስ ታፈሰ ከቆመ ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ መቷት ግብ ጠባቂው የመለሳትን ኳስ ያሬድ ዳርዛ በግንባሩ አመቻችቷት ብሥራት በቀለ ከመረቡ ጋር ባዋሃዳት ኳስ ነበር ጨዋታውን መምራት የጀመሩት።

ከግቧ መቆጠር በኋላ የሀዋሳ ቡድን አባላት ግቡ የተቆጠረበት መንገድ ከጨዋታ ውጭ ነው በሚል ባነሱት ጥያቄ እና በሜዳ ውስጥ በተፈጠሩ እሰጣ ገባዎች ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ከተቋረጠ በኋላ የጀመረው ጨዋታው ሀዋሳ ከተማዎች አቻ ለመሆን ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ በ90+5ኛው ደቂቃ የአቻነቷን ግብ አስቆጥረዋል። በረከት ሳሙኤል በረዥሙ አሻምቷት ሳጥን ውስጥ የነበረው ዓሊ ሱሌይማን ጨርፎ ያስቆጠራት ግብም ኃይቆቹን ከሽንፈት የታደገች ግብ ነበረች።

ከባባድ ጉዳቶች፣ የዋና ዳኛው ደካማ የጨዋታ አመራር ብቃት እና ለጨዋታው መቆራረጥ መነሻ በነበረሩ ተደጋጋሚ እሰጣ ገባዎች ታጅቦ የተካሄደው ጨዋታ በመጨረሻም በአቻ ውጤት ተጠናቋል።