ኢትዮጵያ ቡና ስራ አስኪያጁ አቶ ገዛኸኝ ወልዴን ካሰናበተ በኋላ አዲስ ስራ አስኪያጅ ለመቅጠር ዛሬ ማስታወቂያ ማውጣቱን አስታውቋል፡፡
ባለፉት ወራት ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያስተናግዱ የቆዩት አቶ ገዛኸኝ ባለፈው ሳምንት ከክለቡ እንዲሰናበቱ የተደረገ ሲሆን ዛሬ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በወጣው ማስታወቂያ መሰረት በማኔጅመንት እና ተዛማጅ ዘርፎች ቢኤ ዲግሪ እና ከዛ በላይ እንዲሁም 10 አመት የስራ ልምድ ያለው አልያም በስራ አስኪያጅነት ለ5 አመት የስራ ልምድ ያለው ግለሰብ ማመልከት እንደሚችል ተገልጧል፡፡
ኢትዮጵያ ቡና ከስራ እሰኪያጅ ሹም ሽር በተጨማሪ አዲስ የቴክኒክ ዳይሬክተር ለመቅጠር ከዚህ ቀደም የነበረውን የቴክኒክ ዳይሬክተር የስራ ሃላፊነትን ዝርዝር በማሻሻል ላይ እንደሚገኝም ታውቋል፡፡
ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ተቃውሞ በኋላ ጫና ውስጥ የነበሩት አቶ ገዛኸኝ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የተደረገው ከተቃውሞው ባሻገር በክለቡ ቦርድ እና በደጋፊ ማህበሩ ስብሰባ በተደረሰ ስምምነት መሰረት እንዲሰናበቱ መደረጉን የኢትዮጵያ ቡና ህዝብ ግንኙነት አቶ ሙሉጌታ ደሳለኝ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ከስራ አስኪያጁ ስንብት እና የቴክኒክ ዳይሬክተር ቅጥር ሌላ ተጨማሪ እርምጃዎች እንደማይኖሩም ጨምረው ገልፀዋል፡፡