መረጃዎች | 38ኛ የጨዋታ ቀን

በ10ኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት የሚከናወኑ መርሐግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!

ኢትዮጵያ ቡና ከ አርባምንጭ ከተማ

በሁለት ነጥቦች የሚበላለጡ እና ከሽንፈት ለማገገም ወደ ሜዳ የሚገቡትን ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነው።

በስምንት ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከድል ጋር ከተራራቁ ሦስት ጨዋታዎች ተቆጥረዋል። በውድድር ዓመቱ ሰባት ሽንፈት ካስተናገደው ወልዋሎ በመቀጠል ከነገው ተጋጣሚው አርባምንጭ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ጋር በጋራ አራት ሽንፈቶች በማስተናገድ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ በሂደት የውጤት ማሽቆልቆል ውስጥ በመግባት ላይ ይገኛል። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ መርሐግብሮች ሽንፈት ከማስተናገዱም በላይ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ስምንት ነጥቦች አራቱን ብቻ ማሳካቱም የውጤት ማሽቆልቆሉ ማሳያ ነው።

የቡና የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ለከፋ ትችት የሚዳርገው ባይሆንም በውጤት ደረጃ ግን ቀስ በቀስ እየተንሸራተተ በወራጅ ቀጠናው ውስጥ እንዲገኝ አድርጎታል፤ ይህንን ተከትሎ ቡድኑ ከተከታታይ ሽንፈቶች የሚያንሰራራበት ድል አስፈላጊው ነው።

በአስር ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አርባ ምንጭ ከተማዎች በመቻል ከገጠማቸው ሽንፈት ለማገገም እንዲሁም የደረጃ መሻሻል የሚያስገኝላቸውን ሦስት ነጥብ ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

በፈጣን ሽግግሮች እንዲሁም አጥቂዎቹን ማዕከል ባደረጉ ቀጥተኛ ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት የሚያደርጉት አዞዎቹ እንደ አብዛኞቹ የሊጉ ክለቦች የወጥነት ችግር ይስተዋልባቸዋል። ፋሲል ከነማ እና ባህር ዳር ከተማን በተከታታይ ካሸነፉባቸው መርሐግብሮች ውጭ በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ መሰብሰብ ያልቻለው ቡድኑ እንደ ውጤቱ ሁሉ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴውም ወጥነት ይጎድለዋል። ሆኖም ሦስት ግቦች ካስተናገደበት የመጨረሻው መርሐግብር በፊት በተከናወኑ አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀታቸው ዋነኛ ጥንካሪያቸው ነው።

ከውጤት ፍላጎታቸው በተጨማሪ ከቡድኖቹ የአጨዋወት ዘይቤ መቀራረብ አንጻር ስንመለከተው ጨዋታው ፈጣን ሽግግሮችን ማዕከል ያደረገ እና ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎም ይገመታል።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል ኢያሱ ታምሩ፣ በፍቃዱ ዓለማየሁ እና መላኩ አየለ በጉዳት ምክንያት አይኖሩም። በአርባምንጭ ከተማ በኩል ደግሞ አበበ ጥላሁን በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን ልምምድ የጀመረው ቻርለስ ሪባኑም ለጨዋታ እንደማይደርስ ታውቋል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ18 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን አርባምንጭ ከተማዎች 7 ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይነትን ሲይዙ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ በ6 ጨዋታዎች ረተዋል። የተቀሩት አምስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በጨዋታ ሳምንቱ ብርቱ ፉክክር ይደረግባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ መርሐግብሮች አንዱ የሆነው የጣና ሞገዶቹን እና የዓምና ቻምፒዮኖቹን የሚያገናኘው ጨዋታ በነገው ዕለት ይካሄዳል።

በአስራ አራት ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህር ዳር ከተማዎች በመጨረሻው ሳምንት ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር አቻ መለያየታቸውን ተከትሎ ያመለጣቸውን ወደ መሪዎቹ ይበልጥ የመጠጋት ዕድል በድል ለማማካስ ቻምፒየኑን ንግድ ባንክ ይገጥማሉ።

በመጨረሻው መርሐግብር ላይ በጊዜ ግብ ማስተናገዱን ተከትሎ በአመዛዡ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ የአቻነት ግብ ፍለጋ ተጠምዶ የዋለው ቡድኑ እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ የነበረው መንፈስ እና ፍላጎት በጥሩ ጎኑ የሚታይ ቢሆንም አሁንም የአፈጻጸም ክፍተቱን መቅረፍ አልቻለም። በፈጣን እንዲሁም በተለጠጠ የመስመር አጨዋወት የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የማይቸገረው ቡድኑ በፍጥነት ወደ ድል አድራጊነት ከመመለስ በዘለለ ከዋንጫ ተፎካካሪዎች አንዱ ይሆናል ተብሎ ከሚገመተው ቡድን ጋር በሚደረገው ጨዋታ ድል ማድረግ በነጥብም ሆነ በአሸናፊነት ስነልቦናው ላይ ያለው ጠቀሜታ ትልቅ እንደመሆኑ  ከሌላ ጊዜ በተለየ ጥንቃቄ የተሞላበት አቀራረብ ወደ ጨዋታው ይገባል ተብሎ ይገመታል።

ስድስት ጨዋታዎች አከናውነው ስምንት ነጥቦች የሰበሰቡት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በ14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ከሦስት ጨዋታዎች መልስ ወልዋሎን አሸንፈው ወደ ድል መመለስ ችለው የነበሩት ንግድ ባንኮች ብርቱ ፉክክር በተደረገበት የመጨረሻው መርሐግብር ከኢትዮጵያ መድን ጋር ነጥብ ተጋርተዋል። ሀምራዊ ለባሾቹ በመጨረሻው ጨዋታ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሻለ እንቅስቃሴ አድርገው የግብ ዕድሎች መፍጠር ቢችሉም ደካማው የአጨራረስ ብቃታቸው ከጨዋታው ከአንድ ነጥብ በላይ እንዳይሸምቱ አድርጓቸዋል። በእርግጥ ከመልካም እንቅስቃሴ ባለፈ የፊት መስመር ተሰላፊዎች የአጨራረስ ብቃት በወትሮ ስልነቱ አለመገኘቱ ለአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ ቡድን አንዱ ድክመት ሆኖ መቀጠሉ ባይካድም ጨዋታዎችን የመቆጣጠር አኳኋናቸው እንዲሁም ያላቸው የተጫዋቾች ጥራት አሁንም ትልቅ ግምት እንዲሰጣቸው የሚያስገድድ ነው።

በጣና ሞገዶቹ በኩል የመሃል ተከላካዩ ፍሬዘር ካሳ በቅጣት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን በንግድ ባንኮች በኩልም ሱሌይማን ሃሚድ እና ፉዓድ ፈረጃ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ሆነዋል። ኤፍሬም ታምራት ግን ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታ ዝግጁ ሆኗል።

ክለቦቹ በሊጉ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ የተቀረው አንድ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ንግድ ባንክ አራት ባህር ዳር ከተማ ደግሞ ሦስት ግቦች አስቆጥረዋል።