ገብረመድህን ሃይሌ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሆነው በፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ መመረጣቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ከታማኝ ምንጮች አረጋግጣለች፡፡
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌን ከሃላፊነት ማንሳቱን ዛሬ በይፋ ማስታወቁን ተከትሎ የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎችን እንዲመሩ ጊዜያዊ አሰልጣኝ መምረጡን ቢያስታውቅም የአሰልጣኙን ማንነት ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
ሶከር ኢትዮጵያ ከፌዴሬሽኑ አካባቢ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ የመከላከያውን አሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ ኢትዮጵያ ከሌሶቶ እና ሲሸልስ ጋር የምታደርጋቸውን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች በጊዜያዊነት ይመራሉ፡፡
ከ2004 ጀምሮ መከላከያን በማሰልጠን ላይ የሚገኙት አሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአሰልጣኝ አስራት ሃይሌ ረዳት በመሆን የሴካፋ ዋንጫን ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የአሰልጣኝ ቅጥሩን ዝርዝር ጉዳይ በቅርቡ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡