ሪፖርት | አፄዎቹ ተከታታይ ድላቸውን አሳክተዋል

ፋሲል ከነማ በጌታነህ ከበደ የመጀመሪያ አጋማሽ ብቸኛ ግብ ወልዋሎ ዓ/ዩኒቨርስቲን 1ለ0 ሲያሸንፉ ቢጫዎቹ በአንፃሩ ስምንተኛውን ሽንፈት አስተናግደዋል።

ፋሲሎች ሲዳማ ቡናን ካሸነፈው ስብስባቸው የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ኤፍሬም ኃይሉ፣ ቢኒያም ላንቃሞ እና አንዋር ሙራድ ገብተው ኪሩቤል ዳኜ ፣ ቃልኪዳን ዘላለም እና ማርቲን ኪዛ ሲወጡ ያለፈውን ሳምንት አራፊ የነበሩት ወልዋሎዎች በስምንተኛ ሳምንት በአርባምንጭ ከተማ ከተሸነፈው ስብስብ ሰለሞን ገመቹን በሚራጅ ሰፋ ፣ ጋዲሳ መብራቴን በሱልጣን በርሄ ቦታ ተክተው ቀርበዋል።

የፋሲል ከነማ አንፃራዊ ብልጫን ያስተዋልንበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሀያ አምስት ያህል ደቂቃዎች ቶሎ ቶሎ ወደ ሳጥን የሚደርሱ የሽግግር አጨዋወቶችን ያየንበት ነበር። ወደ ተጋጣሚያቸው ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በመድረስ የተሻለውን ቅርፅ ይዘው መንቀሳቀስ የቻሉት አፄዎቹ ጌታነህ ከበደ በአንድ ለአንድ ግንኙነት ሦስተኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጎልነት ልትቀየር የምችል ያለቀላት ዕድልን ፈጥሮ ናትናኤል ኪዳኔ በያዘበት አጋጣሚ ጎልን በጊዜ ለማግኘት ተቃርበው ነበር።

ረጃጅም የሆኑ ኳሶችን ወደ ተጋጣሚያቸው የተከላካይ መስመር በመጣል ያገኟቸው የነበሩ ኳሶችን ደግሞ ከሳጥን ውጪ ይመቱ የነበሩት ወልዋሎዎች በሁለት አጋጣሚዎች ያደረጓቸው የርቀት ሙከራዎች ኦማስ ኦባሶጊን ብዙም የፈተኑ አልነበሩም።

በንፅፅር ማጥቃቱ ላይ ብልጫ የያዙት ፋሲሎች ሐቢብ መሐመድ ጎል አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጪ ተብላ ከተሸራች በኋላ 23ኛው ደቂቃ በረከት ግዛው ወደ ግራ አድልቶ ሳጥን ለተገኘው ጌታነህ ከበደ የሰጠውን ኳስ አጥቂው ወደ ጎልነት ለውጦ ቡድኑን መሪ አድርጓል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በይበልጥ ተመጣጣኝ አቀራረቦችን የተመለከትን ሲሆን ወደ ጎል የሚደረጉ ትጋቶች የነበሯቸው ግን ፋሲል ከነማዎች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ በቀጠለው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖቾ የተጫዋች ቅያሪን በማድረግ የተመለሱበት ሲሆን አጀማመሩ ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ ይኑርበት እንጂ አፄዎቹ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ማጥቃቱ ላይ የተሻሉ መሆናቸውን እስከ ተወሰኑ ደቂቃዎች ቢያስመለክቱንም ጠንካራ የጎል ሙከራዎች በአጋማሹ ያልተደረጉበት ነበር።

ጨዋታው ሲቀጥል ከስልሳ አምስት ደቂቃዎች በኋላ ቅኝት ውስጥ ለመግባት ጥረት ማድረግ የጀመሩት ወልዋሎዎች 76ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ጎልን ቢያገኙም ከጨዋታ ውጪ ተብላ ተሽራለች። ዳዋ ሆቴሳ ያስቆጠራት እና በኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው ጎሏ መሻሯን ተከትሎ የቡድኑ አባላት በረዳቱ ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

የሚቀራረብ እንቅስቃሴን ነገር ግን የቢጫ ለባሾች መጠነኛ የማጥቃት መነቃቃት በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች የታየ ቢሆንም ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠረች ብቸኛ ጎል ፋሲል ከነማ 1ለ0 አሸንፎ እንዲወጣ ግድ ብሏል። ድሉ ለፋሲል ተከታታይ ድል ሆኖ ሲመዘገብ ደረጃውንም ወደ ስድስት አሻሽሏል። ወልዋሎ በአንፃሩ በአስከፊ የውጤት ጉዞው ቀጥሎ ስምንተኛ ተከታታይ ሽንፈቱን አስመዝግቦ ግርጌ ላይ ተቀምጧል።