የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ ይደረጋሉ፡፡ በጨዋታዎቹ ዙርያ ያጠናቀርናቸውን አጫጭር ዘገባዎች እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ድሬዳዋ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ (ድሬዳዋ)
የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተከታዮቹ ያለውን ርቀት ለማስጠበቅ ወደ ድሬዳዋ አቅንቶ ድሬዳዋ ከተማን ይገጥማል፡፡
በድሬዳዋ ከተማ በኩል ምንም የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን ሁሉም ተጫዋቾች ለጨዋታው ብቁ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
በጊዮርጊስ በኩል ምንያህል ተሾመ በጉዳት ከቡድኑ ጋር ያላቀና ሲሆን ከኤሌክትሪክ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ጉዳት የገጠመው ራምኬል ሎክ ከቡድኑ ጋር ቢጓዝም የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡
ሲዳማ ቡና ከ ሀዲያ ሆሳዕና (ይርጋለም)
የሁለተኛ ዙር አጀማመሩ ያላማረለት ሲዳማ ቡና ወደ ድል ለመመለስ በሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕናን ያስተናግዳል፡፡
በሲዳማ ቡና በኩል ምንም የተጫዋች ጉዳት እንደሌለ የተገለፀ ሲሆን በሀዲያ ሆሳዕና በኩልም ምንም የተጫዋች ጉዳት አልተመዘገበም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በውሰት ወደ ሆሳእና ያመራው አትክልት ስብሃት እስካሁን ከቡድኑ ጋር እንዳልተቀላቀለ ታውቋል፡፡ አትክልት በጥቅማጥቅም ጉዳይ ከክለቡ ጋር መስማማት ባለመቻሉ እስካሁን አዲስ አበባ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡
ሀዋሳ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ (ሀዋሳ)
ወላይታ ድቻ ወደ ሊጉ ካደገ ወዲህ የሁለቱ ጨዋታ ከፍተኛ ፉክክር ያስተናግዳል፡፡ ነገ በሀዋሳ የሚደረገው ጨዋታም በጉጉት ይጠበቃል፡፡ በሀዋሳ ከተማ በኩል የጉዳት እና የቅጣት ዜና ባለመኖሩ በተሟላ ስብስብ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
በድቻ በኩል ተከላካዩ ቶማስ ስምረቱ ጀርባው ላይ በደረሰበት ጉዳት ከዳሽን ጨዋታ ጀምሮ ያልተሰለፈ ሲሆን በነገው ጨዋታ ላይም አይሰለፍም፡፡
– ይህን ጨዋታ ሶከር ኢትዮጵያ በቀጥታ የጽሁፍ ስርጭት ከሀዋሳ ታደርሳችኋለች፡፡
ዳሽን ቢራ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (ጎንደር)
በወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ የሚገኘው ዳሽን ቢራ ወገብ ላይ ከሚገኘው ንግድ ባንክ ጋር ጎንደር ላይ ይፋለማሉ፡፡
ከዳሽን በኩል ከሀድያ ሆሳዕና ጋር በተደረገው ጨዋታ ተጎድቶ የወጣው አስራት መገርሳ ከወላይታ ድቻ ጋር የተደረገው ጨዋታ ያመለጠው ሲሆን ለነገውም ጨዋታ የመድረሱ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው፡፡
በንግድ ባንክ በኩል የተመዘገበ ምንም አይነት ጉዳት አልተመዘገበም፡፡
ደደቢት ከ አዳማ ከተማ (አአ ስታድየም)
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት አዳማ ከተማ እና ደደቢት ወደ ድል ለመመለስ በማለም ወደ ሜዳ ይገባሉ፡፡
በሁለተኛው ዙር ድል ማግኘት ተስኖት ከመሪው የራቀው ደደቢት በነገው ጨዋታ ከጉዳቱ ያገገመው ዳዊት ፍቃዱን ግልጋሎት የሚያገኝ ሲሆን ያሬድ ዝናቡ የነገው ጨዋታ በጉዳት ያመልጠዋል፡፡
በአዳማ ከተማ በኩል ቶጓዊው ጃኮብ ፔንዛ ከቅጣት ተመልሶ በቋሚ አሰላለፉ እንደሚካተት ሲጠበቅ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ የሆነ ተጫዋች የለም፡፡
– ይህን ጨዋታ ነገ ሶከር ኢትዮጵያ በቀጥታ የፅሁፍ ስርጭት ወደ እናንተ ታደርሳለች፡፡
አርባምንጭ ከተማ ከ መከላከያ (አርባምንጭ)
ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ ባልሆነ አቋም ላይ እንደመገኘታቸው የግድ በማሸነፍ ላይ ተመስርተው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
በሁለተኛው ዙር ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ያጠናቀቀው አርባምንጭ ከደሞዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ጭንቅ ውስጥ የገባ ይመስላል፡፡
በቅርቡ ወደ ቀድሞ ክለቡ የተመለሰው እንዳለ ከበደ የተስማማበት የቅጥር ክፍያ ያልተከፈለው በመሆኑ ልምምድ ማቆሙና በነገው ጨዋታም እንደማይሰለፍ ታውቋል፡፡ በተመሳሳይ በቅርቡ ቡድኑን የተቀላቀለው አመለ ሚልኪያስም ክፍያ ያልተፈፀመለት ቢሆንም ወደፊት ይስተካከላል በሚል ተስፋ ልምምድ መስራቱን ቀጥሏል፡፡
መከላከያ ከጉዳቱ ያገገመው በሃይሉ ግርማን ግልጋሎት ቢያገኝም በርካታ አጥቂዎችን ሳይዝ ወደ አርባምንጭ ተጉዟል፡፡ ባዬ ገዛኸኝ በቅጣት ፣ ምንይሉ ወንድሙ ፣ መሃመድ ናስር እና ለህክምና ጀርመን የሚገኘው ሙሉአለም ጥላሁን በጉዳት ከቡድኑ ውጪ የሆኑ ተጫዋቾች ሲሆኑ የቡድኑ አሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌም በሃዘን ምክንያት ከቡድኑ ጋር አልተጓዙም፡፡
ኢትዮጵያ ቡና ከ ኤሌክትሪክ (አአ ስታድየም)
በሁለተኛው ዙር ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ያሸነፈውና ግብ ያላስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና እና በተቃራኒው ሁሉንም ጨዋታ ተሸንፎ ምንም ግብ ያላስቆጠረው ኤሌክትሪክ የ16ኛውን ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ያደርጋሉ፡፡
በቡና በኩል በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ያቡን ዊልያም ከጉዳቱ አገግሞ የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ሲሆን ሌላው ካሜሩናዊ ሲሪል ፋይስም ከመከላከያ ጋር በነበረው ጨዋታ ካጋጠመወ ጉዳት በሚገባ ባለማገገሙ አይሰለፍም ተብሏል፡፡
በህመም ላይ የሚገኙት አሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች በህክምና ምክንያት የነገው ጨዋታ ላይ አይገኙም፡፡
በሌላ በኩል ተከላካዩ ወንድይፍራው ጌታሁን ከቅጣት ተመልሶ ወደ ቋሚ አሰላለፉ ይመለሳል፡፡
– ይህን ጨዋታ ነገ ሶከር ኢትዮጵያ በቀጥታ የፅሁፍ ስርጭት ወደ እናንተ ታደርሳለች፡፡
የ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች
ማክሰኞ ሚያዝያ 25 ቀን 2008
09፡00 ድሬዳዋ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ (ድሬዳዋ)
09፡00 ሲዳማ ቡና ከ ሀዲያ ሆሳዕና (ይርጋለም)
09፡00 ሀዋሳ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ (ሀዋሳ)
09፡00 ዳሽን ቢራ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (ጎንደር)
09:00 ደደቢት ከ አዳማ ከተማ (አአ ስታድየም)
09፡00 አርባምንጭ ከተማ ከ መከላከያ (አርባምንጭ)
11፡30 ኢትዮጵያ ቡና ከ ኤሌክትሪክ (አአ ስታድየም