በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ “ለ” ተካፋይ የሆኑ ሁለት ቡድኖች አሰልጣኞቻቸውን በውጤት ማጣት መነሻነት አሰናብተዋል።
የ2017 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር በአዲስ አበባ እና በሀዋሳ ከተሞች ላይ እየተደረጉ ይገኛል። በምድብ “ለ” የተደለደሉ ቡድኖች እየተወዳደሩባት የምትገኘው ሀዋሳ ከተማ የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎችን ከትናንት ጀምሮ ማስተናገድ የጀመረች ሲሆን በዛሬው ዕለትም የሁለተኛ ቀን መርሐግብር ሲቀጥል ሁለት ቡድኖች ዋና አሰልጣኞቻቸውን ከኃላፊነት በማሰናበት በረዳት አሰልጣኞች እየተመሩ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
8 ሰዓት ላይ ኦሜድላን የሚገጥመው ስልጤ ወራቤ ባለፈው የውድድር ዘመን አጋማሽ ላይ ከሻሸመኔ ጋር የተለያዩትን አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙን በመቅጠር ሲመራ የቆየ ሲሆን አሰልጣኙ ካደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች ስድስት ነጥቦች ብቻ ይዘው በደረጃ ሰንጠረዡ 9ኛ ላይ በመቀመጣቸው ለመሰናበት የተገደዱ ሲሆን በተመሳሳይ በዛሬው ዕለት ከየካ ክፍለ ከተማ ጋር የሚጫወቱት አክሱም ከተማዎችም በተመሳሳይ የውጤት ችግር የተነሳ ቡድኑ በሰንጠረዡ አስረኛ ላይ በ5 ነጥቦች በመቀመጡ ከቀድሞው የአዳማ ከተማ ፣ ስሑል ሽረ ፣ ሼር ኢትዮጵያ ፣ ደሴ ከተማ እና በድጋሚ አክሱምን ከመሩት አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃም ጋር እንደተለያዩ ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ አመላክቷል።