ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ እና ፈረሰኞቹ ያለ ያለ ጎል ጨዋታቸውን ፈጽመዋል

የዕለቱ ቀዳሚ የነበረው የባህርዳር ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ያለ ጎል 0ለ0 በሆነ የአቻ ውጤት ተቋጭቷል።

ባህርዳሮች በኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ድላቸው ላይ ያልነበረው ፍሬዘር ካሳን በወንድወሰን በለጠ ብቻ ሲለውጡ በመቻል ሽንፈት አስተናግደው የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው በሦስት ተጫዋቾች ላይ ቅያሪን ሲያደርጉ ባህሩ ነጋሽ ፣ አብዱ ሳሚዮ እና ክዋሜ ፍሪምፓንግ ወጥተው ተመስገን ዮሐንስ ፣ በረከት ወልዴ እና ፍዓድ አብደላ በምትኩ በቋሚ አሰላለፍ ተካተው ገብተዋል።

በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በአምላክ ተሠማ መሪነት የጀመረው የመጀመርያው አጋማሽ የአማካይ ክፍል ብልጫ የነበራቸው ፈረሰኞቹ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች የፈጠሩበት የጣና ሞገዶቹ ደግሞ የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር የተቸገሩበት ነበር።

ከአማካይ ክፍል ብልጫው በዘለለ በመስመሮች በኩል በሚደረጉ ጥረቶችን የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጨዋታው 8ኛው ደቂቃ በፈጣን ሽግግር የባህርዳር ሦስተኛው ሜዳ ደርሰው አማኑኤል አረቦ ከግብ ዘቡ ፔፕ ሰይዶ ጋር በአንድ ለአንድ ግልፅ የማግባት ዕድልን ቢያገኝም በአይቮሪያኑ አስደናቂ ብቃት ኳሷ ከግብነት መክናለች።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ይበልጥ እየተሻሻሉ በመጡባቸው የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በርከት ያሉ ዕድሎች ማግኘት ቢችሉም ኳስና መረብ ማገናኘት አልቻሉም። ቡድኑ ከፈጠራቸው ሙከራዎችም ቢንያም ፍቅሬ በሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ መሬት ለመሬት መቶት አማኑኤል ኤርቦ ወደ ግብነት ያልቀየረው እንዲሁም ፉዐድ አብደላ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ያመከነው እና ፍፁም ጥላሁን ከአማኑኤል እና ቢንያም የአንድ ሁለት ቅብብል በኋላ አግኝቷት አዙሮ በመምታት ዒላማዋን ሳትጠብቅ የወጣችው ኳስ ፈረሰኞቹን ቀዳሚ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

የጣና ሞገዶቹ በበኩላቸው በተለይ በቸርነት ጉግሳ በተሰለፈበት የቀኝ መስመር በኩል የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም የመጨረሻው ሜዳ ክፍል ላይ የነበራቸው ድክመት የጠራ የግብ ዕድል እንዳይፈጥሩ አድርጓቸዋል።

ከዕረፍት ተመልሶ የቀጠለው ጨዋታ መጠነኛ መቀዛቀዞችን በአጀማመሩ ያስመለከተን ቢሆንም ቀስ በቀስ ሽግግሮችን ተበራክተው ነገር ግን ጥራት ያላቸው የጎል ሙከራዎችን ያላስተዋልንበት ጭምር ነበር። በአጋማሹ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በጉዳት ባህርዳር ከተማ ፍሬዘር ካሳን በወንድወሰን በለጠ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው ቶሎሳ ንጉሴን በሔኖክ ዮሐንስ የተኩባቸው ለውጦች ምንአልባትም በጨዋታው በልዩነት ሊነሱ የሚችሉ ክስተቶች ካልሆኑ በስተተቀር ጨዋታው ግለቱ ወረድ ያለ መልክ ነበረው።

ከራስ ሜዳ በሚደረጉ ንክኪዎች ሦስተኛው ሜዳ ላይ በቶሎ መድረስን አልመው ቡድኖቹ ቢንቀሳቀሱም የመጨረሻው ሜዳ ላይ የሚታዩ ተደጋጋሚ የስልነት ችግሮች በጨዋታው ላይ ዕድሎች በበቂ ሁኔታ ተፈጥረው እንዳንመለከት ዳርጓል። 68ኛው ደቂቃ የጣናው ሞገድ በጥሩ ቅብብል ሳጥን ደርሰው ፍፁም ጥላሁን በግብ ጠባቂው ተመስገን የተያዘበት እንዲሁም በመጀመሪያው አጋማሽ ዕድሎችን በማግኘት የተዋጣላቸው ፈረሰኞቹ 70ኛው ደቂቃ በመሐመድ ኮኔ ከሳጥን ውጪ ካደረጓት ሙከራ በቀር በበቂ መልኩ አጋጣሚዎች በጨዋታው አልተፈጠሩበትም። ባህርዳር ከተማዎች ከቆሙ እና መሳይ አገኘሁ ከጀርባ በሚመነጩለት ኳሶች ብልጫውን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ቢወስዱም በዕድሎች አይናፋርነት  ያጠቃው ጨዋታ ያለ ጎል 0ለ0 ተቋጭቷል።