ሪፖርት | ነብሮቹ በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ 5ኛ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል

በግቦች በተንበሸበሸው የምሽቱ ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕናዎች በስል የመልሶ ማጥቃት ሲዳማ ቡናን በመርታት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ያሉበትን ውጤት አስመዝግበዋል።

በመጨረሻ ጨዋታቸውን አዳማ ከተማን የረቱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ቃለዓብ ውብሸትን በሄኖክ አርፊጮ ተክተው ሲቀርቡ በአንፃሩ በውጤት አልባ ጉዞ ላይ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች በድሬዳዋ ከተማ ከተረታው የመጀመሪያ 11 ተሰላፊዎች ውስጥ ባደረጓቸው አራት ለውጦች ቶማስ ኢካራ ፣ጊት ጋትኩት ፣ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን እና ይገዙ ቦጋለ አስወጥተው በምትካቸው መክብብ ደገፉ ፣ ኢማኑኤል ላርዬ ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ እና ፍራኦል መንግሦቱን ቀይረው ቀርበዋል።

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ከፍ ያለ ጫና አሳድረው መጫወት የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች የነበሩ ቢሆንም ሀዲያ ሆሳዕናዎቹ በ7ኛው ደቂቃ በግሩም የመልሶ ማጥቃት መሪ መሆን ችለዋል ፤ የሀዲያ ሆሳዕናው የፊት አጥቂ እዮብ ዓለማየሁ በመልሶ ማጥቃት ከራሱ የሜዳ አጋማሽ ወደ ሲዳማ ቡና ሳጥን እየነዳው ያደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ የሲዳማ ተከላካዮች ሲደረቡ በቅርብ ርቀት የነበረው ተመስገን ብርሃኑ ኳሷን ከመረብ አዋህዶ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

ምንም እንኳን ቅድሚያ ቢወሰድባቸውም አሁንም ቢሆን አውንታዊነታቸውን ያስቀጠሉት ሲዳማ ቡናዎች በ16ኛው ደቂቃም በድንገት ሁለተኛ ግብ አስተናግደዋል ፤ የሲዳማ ቡናው የግብ ዘብ መክብብ ደገፉ ስህተት መነሻ ባደረገ የሀዲያ ማጥቃት ሂደት እዮብ ዓለማየሁ የቡድኑን ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል።

ምንም እንኳን በርካታ ግማሽ ዕድሎችን በመፍጠር ሲዳማ ቡናዎች አንፃራዊ የበላይነት በነበራቸው የመጀመሪያ አጋማሽ ሀዲያ ሆሳዕናዎች በተደጋጋሚ በመልሶ ማጥቃት ግን አደጋ ለመደቀን ጥረት ሲያደርጉ አስተውለናል።

በ38ኛው ደቂቃ የሲዳማ ቡናው የመስመር ተከላካይ ብርሃኑ በቀለ የሀዲያውን አጥቂ እዮብ ዓለማሁን የጋራ ኳስን ለማሸነፍ ካደረጉት ፍትጊያ በኋላ ከኳስ ውጭ ተጫዋቹን በመማታቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።

በግቦች ባይታጀብም በተሻለ መንገድ በአጋማሹ የተንቀሳቀሱት ሲዳማ ቡናዎች በ41ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳሊሶ ከሀዲያ ሳጥን ጠርዝ ያገኙትን ቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን ወደ ጨዋታ ልትመልስ የምትችል ግብን ከመረብ አሳርፉ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸውን ተነሳሽነት በማስቀጠል የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች በ54ኛው ደቂቃ የአቻነቷን ግብ ከመረብ አሳርፈዋል ፤ ሳሙኤል ሳሊሶ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ሳጥን ውስጥ የነበረው ደስታ ደሙ በግንባሩ ገጭቶ ማስቆጠር ችሏል።

በግቦች በተንበሸበው ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ዳግም መሪ ለመሆን ሰባት ደቂቃ ብቻ ነበር ያስፈለጋቸው ፤ በጨዋታው ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ተመስገን ብርሃኑ ሀዲያ ሆሳዕናዎች በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ካቋረጡት ኳስ የተነሳውን የመልሶ ማጥቃት በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮ ቡድኑን ዳግም ቀዳሚ አድርጓል።

መሪ በሆኑ በደቂቃዎች ልዩነት ብሩክ በየነን አስወጥተው በየነ ባንጃን ያስገቡት ሀዲያዎች ጨዋታውን በተወሰነ መልኩ በማቀዝቀዝ በእጃቸው የገባውን መሪነት አሳልፈው ላለመስጠት ጥረት አድርገዋል።

ይህም ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ጨዋታው 3-2 ማሸነፍ ሲችሉ ይህም የውድድር ዘመኑ አምስተኛ ተከታታይ ድላቸው ሆኖ ተመዝግቧል በአንፃሩ የሲዳማ ቡና ውጤት አልባ ጉዞ አሁንም እንደቀጠለ ነው።