በ11ኛ ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ዕለት የሚከናወኑ መርሃግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ወላይታ ድቻ ከ አዳማ ከተማ
ከአቻ እና ከሽንፈት መልስ የሚገናኙ በአራት ነጥቦች የሚበላለጡ ቡድኖች ወደ ድል መንገድ ለመምጣት የሚያደርጉት ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ያልቀመሱት ወላይታ ድቻዎች በአስራ አምስት ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ከሦስት ተከታታይ ድሎች መልስ በሦስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተው የወጡት የጦና ንቦች ዳግም ወደ ድል ለመመለስ አዳማን ይገጥማሉ። ተከታታይ ድሎች ያመዘገቡበት
አስደናቂ ግስጋሴ ለማስቀጠል እየተቸገሩ የሚገኙት የጦና ንቦቹ አሁንም ቢሆን በስድስት መርሃግብሮች ከሽንፈት መራቃቸው እንደ አውንታ የሚነሳላቸው ነጥብ ቢሆንም ዳግም ወደ ድል ለመመለስ በቅርብ ሳምንታት የተስተዋሉባቸው የማጥቃት ውስንነቶች መቅረፍ ግድ ይላቸዋል።
ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደው ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ እጅግ ጠንካራ ቢሆንም ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ አሁንም ውስንነት አለበት። በነገው ጨዋታም
ከተጋጣሚያቸው የመከላከል ጥንካሬ አንፃር ቀለል ያለ ፈተና ይጠብቃቸዋል ተብሎ ቢገመትም የማጥቃት አጨዋወቱ አሁንም ለውጦች እንደሚፈልግ ይታመናል።
በአስራ አንድ ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች በሀድያ ሆሳዕና ከገጠማቸው ሽንፈት ለማገገም በስድስት ጨዋታዎች ሽንፈት ያልቀመሱት ወላይታ ድቻዎች ይገጥማሉ።
አዳማ ከተማዎች በመጨረሻው ጨዋታ ኳሱን በተሻለ አኳኋን ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርጉም በመከላከሉ ረገድ የነበራቸው ግለሰባዊ እና መዋቅራዊ ግድፈቶችን ለሽንፈት ዳርጓቸዋል።
ቡድኑ ኳሱን ከግብ ጠባቂው መስርቶ ለመጫወት በሞከረባቸው ጨዋታዎች በቅብብል ስህተቶች ተጋላጭ እየሆነ ይገኛል። በተጠቀሰው ችግር በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ግብ ማስተናገዱም የዚህ ማሳያ ነው። ይህንን ተከትሎ በነገው ጨዋታ መሰል ክፍተቶችን ከማረም ባለፈ በግብ መታጀብ ያልቻለው ተስፋ ሰጪ የማጥቃት አጨዋወታቸውን የአፈፃፀም ክፍተት ማረም ግድ ይላቸዋል።
በወላይታ ድቻ በኩል ያለፉት ጨዋታዎች በጉዳት ያልነበሩት ፍፁም ግርማ እና ብዙዓየሁ ሰይፉ ወደ ልምምድ ቢመለሱም ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው በአሰልጣኙ የሚወሰን ሲሆን የተቀረው የቡድኑ ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በአዳማ ከተማ በኩል ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ከጉዳት ሲመለስ ቢኒያም ዐይተን ረጅም ጉዳት ላይ ያለው ዳንኤል ደምሱ እና ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ በጉዳት ተከላካዩ ፍቅሩ ዓለማየሁ ደግሞ በቅጣት በነገው ጨዋታ አይሰለፉም።
ቡድኖቹ 20 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ 9 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን አዳማ ከተማ 7 ጨዋታ አሸንፏል። ቀሪው አራት ጨዋታ ደግሞ አቻ ተጠናቋል። ድቻ 22፣ አዳማ 18 አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን አልተካተተም)
ኢትዮጵያ ቡና ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ
ከተከታታይ ሽንፈቶች መልስ ድል ያደረጉት ቡናማዎቹ የመጀመርያው ነጥብ ለማስመዝገብ በመጠባበቅ ላይ ካሉት ቢጫዎቹ የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሀ-ግብር ነው።
በአስራ አንድ ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከተከታታይ ሽንፈቶች መልስ አዞዎቹ ላይ የተጎናፀፉትን ድል ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በውድድር ዓመቱ ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ እየተቸገሩ የሚገኙት ቡናማዎች በአንፃራዊነት ቀለል ያለ ተጋጣሚ በሚያገኙበት የነገው መርሀ-ግብር ድል ማድረግ የደረጃ መሻሻል ያስገኝላቸዋል። ቡድኑ በውጤትም ሆነ በእንቅስቃሴ የወጥነት ችግር ቢስተዋልበትም ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ መረቡን ሳያስደፍር ድል ካደረገበት ማግስት ወደ ነገው ጨዋታ መቅረቡ በስነ ልቦና ረገድ ያለው ጠቀሜታ ላቅ ያለ ነው።
በሦስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ማስቆጠር ችሎ የነበረው ቡድኑ የተሻሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ባሳየበት የመጨረሻው መርሃግብር ሁለት ግቦች ማስቆጠር ችሏል፤ በነገው ዕለትም በሊጉ በጨዋታ በአማካይ 1.6 ግቦች ላስተናገደው የወልዋሎ የመከላከል አደረጃጀት ፈተና እንደሚሆን እሙን ነው። በጥቅሉ ሲታይ የደረጃ ልውውጥ በበረከተበት ሊግ ተከታታይ ድል ማስመዝገብ ያለው ጠቀሜታ ላቅ ያለ በመሆኑ ከፍ ባለ ትኩረት ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል።
በዜሮ ነጥብ በሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኙት ወልዋሎዎች
የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ነጥብ ለማስመዝገብ የነገውን ጨዋታ ይጠብቃሉ።
ወልዋሎ ከመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች አንፃር ሲታይ በእንቅስቃሴ ደረጃ መሻሻል እያሳየ ቢሆንም አሁንም ነጥብ ማስመዝገብ ያልቻለው የሊጉ ብቸኛ ክለብ ሆኖ ለመቀጠል ተገዷል።
ከውጤቱም ባሻገር በመከላከሉም ይሁን በማጥቃቱ ረገድ ደካማ ቁጥሮች ያስመዘገበው ቡድኑ በሊጉ ሁለት ግቦች በማስቆጠር እንዲሁም አስራ ሦስት ግቦች ማስተናገዱ ያለበትን ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ቢጫዎቹ ከአሰልጣኝ ለውጡ በኋላ በተከናወኑ ጨዋታዎቹ በተለይም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተሻለ መነሳሳት ለመንቀሳቀስ ሲሞክሩ ታይተዋል። በነገው ጨዋታ ውስን ተስፋዎች የታየበት እንቅስቃሴ ለማሳደግ ሙሉ ጨዋታ በተሻለ የትኩረት ደረጃ ለመከወን የሚያስችላቸውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በነገው ዕለት ከቡድኑ ጋር ሦስተኛ የሊግ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት አሰልጣኝ ፀጋዬ በቀዳሚነት በግለሰባዊ ስህተቶች የጎላው የመከላከል አደረጃጀታቸው ድክመት መቅረፍ ይኖርባቸዋል። ተደጋጋሚ ሽንፈት የወለደው የሥነ ልቦና ስስነት የሚታይበት ቡድኑ በነገው ዕለት ከድል ጋር የሚታረቅ ከሆነ ችግሩ ይቀረፍ ይሆን ብለን እንድንጠብቅ ያደርገናል።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል ኮንኮኒ ሀፍዝ ፣ በፍቃዱ ዓለማየሁ እና መላኩ አየለ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ ሌላኛው ጉዳት ላይ የነበረው ኢያሱ ታምሩ ግን ተመልሷል። በወልዋሎ በኩል አምበሉ በረከት አማረ ቅጣቱን ጨርሶ የቀድሞ ክለቡን ለመግጠም ዝግጁ ቢሆንም ከጉዳት መልስ ቡድኑን የተቀላቀለው ናትናኤል ዘለቀ የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው።
የተሰረዘው የ2012 ውድድር ዓመት ጨዋታ ሳይጨምር በሊጉ ለአራት ጊዜያት የተገናኙት ቡድኖቹ ኢትዮጵያ ቡና 3 በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። በቀሪው አንድ ጨዋታ ደግሞ ወልዋሎ ድል አስመዝግቧል። ቡና 4 ሲያስቆጥር ወልዋሎ 2 አስቆጥሯል።