ሪፖርት | የመዲናይቱን ቡድኖች ያገናኘው ጨዋታ ያለ ጎል ተቋጭቷል

የመቻል እና ኢትዮጵያ መድን ጨዋታ 0ለ0 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል።

መቻሎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ድል ከተቀናጀው ስብስብ ዓለምብርሀን ይግዛውን በዳዊት ማሞ የተኩበት ብቸኛ ለውጣቸው ሲሆን አራፊ ከመሆናቸው በፊት ከንግድ ባንክ ጋር ነጥብ ተጋርተው የነበሩት መድኖች ግን የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ አዲስ ተስፋዬን በሚሊዮን ሠለሞን ፣ መሐመድ አበራን በአቡበከር ሳኒ ተክተዋል።

መሐል ሜዳ ላይ በአመዛኙ የሚደረጉ ንክክኪዎች በመጀመሪያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ያስመለከተን ጨዋታ የመቻሎችን ከሳጥን ሳጥን የሚደረጉ ትጋቶችን ያስተዋልንበት ነበር። 11ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ተሻምቶ በተከላካዮች ተጋጫጭታ ሳጥን ጠርዝ ላይ በረከት ደስታ አግኝቶ አክርሮ መቷት የግብ ዘቡ አቡበከር ኑራ በጥሩ ቅልጥፍና ባወጣበት ሙከራን የሰነዘረው ቡድኑ በቀጣዮቹም ደቂቃዎች በድግግሞሽ ሦስተኛው ሜዳ ላይ ያደርሳቸው የነበረውን እንቅስቃሴ ቢያደርጉም በቀላሉ ወደ ግብነት መቀየሩ ላይ ግን ውስንነቶች ታይቶባቸዋል።

ጨዋታው ሲቀጥል መድኖች ከራስ ሜዳ በሚያደርጓቸው ቅብብሎች ረጃጅም በሆኑ መነሻቸውንም ከመስመር በማድረግ መንቀሳቀስን መርጠው ቢጫወቱም በአጋማሹ የፈጠሯቸውን ዕድሎች በፍፁም አልነበሩም። ወደ መልበሻ ክፍል ጨዋታው ሊያመራ በተቃረበባቸው የመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ውስጥ የሽግግር አጨዋወትን ከፍ ባለ ግለት ቡድኖቹ ሲጠቀሙ ቢስተዋልም አሁንም የመጨረሻው ሜዳ ላይ ብልጫውን የወሰዱት ጦረኞች ናቸው።  ሽመልስ በቀለ ራሱ ላይ በተሰራ ጥፋት ከቀኝ የሜዳው ሳጥን ጠርዝ ከተገኘ ቅጣት ምት ሞክሮ አቡበከር የያዘበት እና 34ኛው ደቂቃ በክፍት ጨዋታ ሽመልስ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ አቡበከር ፈጥኖ የያዘበት የቡድኑ ሊያስቆጩ የሚችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ከዕረፍት ተመልሶ የቀጠለው ጨዋታ በይበልጥ ቡድኖቹ ከደቂቃ ደቂቃ የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን ለመውሰድ ከሚያደርጉት ጥረት ውጪ በሙከራዎች መድመቅ የተሳነው ነበር። በመጀመሪያው ከነበራቸው ወረድ ያለ አቀራረብ በሁለተኛው አጋማሽ መሻሻሎችን ያሳዩት መድኖች ከመስመር በመነሳት ያደረጉ በነበረው እንቅስቃሴ 53ኛው ደቂቃ ጎል ለማስቆጠር ተቃርበዋል።


ከቀኝ በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ወገኔ ገዛኸኝ በአንድ ለአንድ ግኑኝነት የግብ ዘቡ አሊዮንዜ ናፊያንን ጭምር በማለፍ ያለቀለት ዕድልን አግኝቶ ወደ ውጪ የወጣችበት በአጋማሹ በልዩነት የጎላችዋ ጠጣሯ ሙከራ ነበረች። በይበልጥ እንቅስቃሴ ላይ ትኩረትን አድርጎ በበቂ ሁኔታ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ጨዋታው በመቻል በኩል ሽመልስ እና ተቀይሮ የገባው ዳንኤል ካገኟቸው የመጨረሻ ደቂቃ ክፍት አጋጣሚዎች በስተቀር የጠሩ ሙከራዎችን ሳንመለከት ያለ ጎል ጨዋታው ተቋጭቷል።