ሀድያ ሆሳዕና ከረጅም ጊዜ ጉዳት ተመልሶ የመጀመሪያ ጨዋታውን ባደረገው ጫላ ተሺታ ብቸኛ ጎል መቻልን 1ለ0 በመርታት የሊጉን ተከታታይ ስድስተኛ ድል አሳክተው የሊጉን መሪነት ተቆናጠዋል።
ከሊጉ መቋረጥ በፊት መቻሎች ከኢትዮጵያ መድን ጋር ያለ ጎል ያጠናቀቀው ቡድናቸው ላይ ለውጥን ሳያደርጉ ሲገቡ በአንፃሩ ሀድያ ሆሳዕና ሲዳማ ቡናን ድል ካደረገው ስብስብ ውስጥ ጉዳት ባስተናገደው ተመስገን ብርሀኑ ከጉዳት በተመለሠው እና ለመጀመሪያ ጊዜ ጨዋታን ለማድረግ ወደ ቋሚነት በመጣው ጫላ ተሺታ በብቸኝነት ተተክቷል።
የሳምንቱ መቋጫ በሆነው እና ላቅ ያለውን ፉክክር ማስመልከቱን ከጅምሩ እያሳየን የቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች መቻሎች ኳስን በአንድ ሁለት ንክኪ በቀላሉ የተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ መገኘት ቢችሉም ጠጣሩን የሀድያ ሆሳዕና የኋላ ክፍል ማስከፈቱ ከብዷቸው ተመልክተናል።
15ኛው ደቂቃ ላይ ከሽመልስ መነሻዋን ያደረገች ኳስን በረከት ታግሎ አቀብሎት አብዱልከሪም ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ የግቡን ቋሚ ብረት ታካ ለጥቂት የወጣችዋ በቡድኑ የተደረገች ቀዳሚዋ ሙከራ ሆናለች። እንደነበረው ፈጣን አቀራረብ በግብ ሙከራዎች መድመቅ ባልቻለው ጨዋታ አካፋይ ሰዓትን ሲሻገር በይበልጥ ተመጣጣኝ የሆነውን እንቅስቃሴ ብንመለከትም ሀድያ ሆሳዕናዎች በፈጣን ሽግግር ወደ መስመር ዘንበል ብለው መጫወትን መርጠው በተንቀሳቀሱበት ወቅት መሪ ያደረገቻቸውን ጎል አግኝተዋል።
29ኛው ደቂቃ ላይ መሐል ሜዳ የተገኘው እዮብ ዓለማየሁ ከተከላካይ ጀርባ ወደ ቀኝ የሳጥኑ ጠርዝ የጣለውን ኳስ ጫላ ተሺታ በደረቱ አቀዝቅዞ አሊዮንዚ ናፊያን መረብ ላይ ከረጅም ጊዜ ጉዳት ተመልሶ ባደረገው የሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ላይ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። ሜዳ ላይ ይደረጉ ከነበሩ እንቅስቃሴዎች በስተቀር አጋጣሚዎች በበቂ መልኩ ያልተመለከትንበት ቀሪዎቹ ደቂቃዎች ነብሮቹን መሪ እንዳደረገ ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።
ሀድያ ሆሳዕናዎች እዮብ ዓለማየሁን በሳሙኤል ዮሐንስ ከለወጡ በኋላ ከዕረፍት መልስ የቀጠለው ጨዋታ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር የተቀዛቀዝ አጀማመር ቢኖረውም ከደቂቃ መጋመሶች በኋላ ግን የመቻሎች ብልጫ የተስተዋለበት ነበር። በይበልጥ ለሳጥን የተጠጋውን እንቅስቃሴ ያዘወተሩት እና ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያለማመንታት የተሻለውን ጊዜ ያሳለፉት ጦሮቹ በተለይ በበረከት እና ሽመልስ ጥምረት ወደ አቻነት ለመመለስ ትጋት ባይለያቸውም የሀድያ ሆሳዕናን የተጠቀጠቀ መከላከል አልፎ መረቡን ማግኘቱ ግን ቀላል አልሆነላቸውም።
ይሁን እንጂ በረከት ከሽመልስ ጋር በፈጠረው ጥሩ መናበብ ሽመልስ ከግራው የማጥቂያ ሳጥን በኩል በሁለት አጋጣሚዎች በተመሳሳይ በአንድ ለአንድ ግንኙነት ያለቀላቸውን ዕድሎች አግኝቶ የነበረ ቢሆንም በግብ ዘቡ ያሬድ በቀለ ንቃት ተመልሰዋል። 72ኛው ደቂቃ ላይ የስታዲየሙ ፓውዛ ለሁለት ደቂቃዎች ብቻ ጠፍቶ ከተመለሰ በኋላ ጨዋታው ሲቀጥል ያስቆጠሯትን አንድ ግብ በማስጠበቅ አሸንፎ ለመውጣት የተጋጣሚያቸውን ጫና መቋቋም ላይ ያተኮረውን እንቅስቃሴ ብቻ መርጠው ይጫወቱ የነበሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች በመጨረሻም ተሳክቶላቸው 1ለ0 በማሸነፍ የሊጉ ተከታታይ ስድስተኛ ድላቸውን አስመዝግበዋል።