ሪፖርት | የጄሮም ፊሊፕ አስደናቂ ጎል ለባህርዳር ጣፋጭ ድል አስገኝቷል

ሁለቱን የውሀ ዳር ከተሞች ያገናኘው የጣናው ሞገድ እና ኃይቆቹ መርሐ-ግብር በባህርዳር ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሀዋሳዎች በፋሲል ከነማ ጨዋታ ላይ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ውስጥ በረከት ሳሙኤል እና እንየው ካሳሁንን በሲሳይ ጋቾ እና ወንድማገኝ ማዕረግ ሲተኳቸው ባህርዳሮች ግን ከድሬዳዋ ከተማ ጋር 1ለ1 የወጣውን ሙሉ ቡድን በመያዝ ለጨዋታው ቀርበዋል።

ሁለቱን የውሀ ዳር ከተሞች ያገናኘው የሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ በማጥቃቱ ባህርዳር ከተማዎች የተሻሉ ቢሆንም የግብ አጋጣሚን በመፍጠሩ ሀዋሳዎች ቀዳሚ ነበሩ። 5ኛው ደቂቃ ዳዊት ታደሠ ከመሐል ሜዳ የመታውን በተከላካዮች ተደርባ ኳሷ ስትመለስ ዓሊ ሱለይማን ቢሞክራትም በቀላሉ የግብ ዘቡ ፔፕ ሰይዶ ይዞበታል።

ጨዋታውን በአግባቡ በመቆጣጠር ተደጋጋሚ ሙከራዎችን መሰንዘር የጀመሩት ባህርዳር ከተማዎች ፍሬው ሠለሞን ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ፍሬዘር ካሳ በግንባር ገጭቶ በግቡ አግዳሚ ብረት በኩል ልትወጣ የቻለችበት በተለይ 15ኛው ደቂቃ አምሳሉ ጥላሁን ከቀኝ መስመር በኩል ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ከአንድ ንክኪ በኋላ ያገኘው ሙጂብ ቃሲም ቢመታውም ግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ ባህርዳሮችን መሪ ለማድረግ የተቃረበችዋን ኳስ በጥሩ ብቃት አምክኗታል።

ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ደርሶ አንዳች ነገርን ከአጋማሹ ለማስመዝገብ የሚታትሩት የጣናው ሞገድ 20ኛው ደቂቃ መሳይ አገኘው ከመስመር ወደ ውስጥ ያሻማትን የሰይድ ሀብታሙ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ታክሎበት ነፃ ሆኖ ኳሷን ያገኘው ወንድወሰን በለጠ ክፍቷን ዕድል ሳይጠቀም ሲቀር ቁመታሙ አጥቂ ጄሮም ፊሊፕ ከደቂቃ በኋላ ሌላ ዕድልን ፈጥሮ በሰይድ ሀብታሙ ቅልጥፍና ተመልሳበታለች።

የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ለመውሰድ ከሚታዩ ፍልሚያዎች በስቀር በግብ ሙከራዎች ያልታጀበው ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ከረጅም ደቂቃዎች በኋላ ሀዋሳዎች ሁለተኛዋን ሙከራ 31ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። ከቀኝ መስመር ሲሳይ ጋቾ የሰጠውን ኳስ ቢኒያም በላይ ወደ ውስጥ ሲያሻግር እስራኤል እሸቱ ገጭቶ በግቡ ቋሚ የግራ ብረት በኩል ወጥቶበታል። 37ኛው ደቂቃ የሀዋሳው ተከላካይ ወንድማገኝ ማዕረግ ከራስ ሜዳ ተጫዋቾችን አልፎ ለመውጣት ጥረት ሲያደርግ ሙጂብ ነጥቆት ያደረጋት ሙከራ 43ኛው ደቂቃ ጄሮም ፊሊፕ ከቅጣት ምት መቶ ሰይድ የመለሰበት እንዲሁም ደግሞ በጭማሪ ደቂቃ ቢኒያም ለሀዋሳ ፍፁም ለባህርዳር ጥሩ አጋጣሚዎችን ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

መጠነኛ መቀዛቀዝን በአጀማመሩ ያሳየን እንጂ የባህርዳር ከተማን የተሻለውን እንቅስቃሴ በሂደት ያስተዋልንበት ሁለተኛው አጋማሽ ቡድኑ በይበልጥ በሽግግር አጨዋወት በሚንቀሳቀስበት ወቅት እጅግ ለግብ የቀረቡ ጥቃቶችን በተጋጣሚው ላይ ሰንዝሯል። 54ኛው ደቂቃ በጥሩ የእግር ስራ ከሳጥን ውጪ ፍፁም ዓለሙ አክርሮ መቶ ሰይድ በተቆጣጠረበት ቅፅበት ጥቃትን መሰንዘር የጀመረው ቡድኑ ከዚህች አጋጣሚ በኋላም በድግግሞሽ የሀዋሳን ሳጥን ጎብኝቷል።

ረጃጅም ኳሶቻቸው ይባክኑባቸው የነበሩት እና ስልነት የሚጎላቸው ሀዋሳዎች 73ኛው ደቂቃ እጅጉን አደገኛ ሙከራን ሲያደርጉ ቢኒያም በላይ ከቅጣት ያሻማውን ኳስ እስራኤል እሸቱ በግንባር ገጭቶ የግቡ የቀኝ ቋሚ ብረትን ኳሷ ገጭታ ስትመለስ በተከላካዮች መራቅ የተሳናትን ኳስ ዳግም ያገኘው ሠለሞን ወዴሳ በግብ ዘቡ ፔፕ ሰይዶ ጥረት ተይዛበታለች። ያለ መታከት ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት ብርቱ ጥረት ያልተለያቸው ባህርዳሮች 80ኛው ደቂቃ የአሸናፊነት ግባቸውን ወደ ቋታቸው ከተዋል።

ጄሮም ፊሊፕ ከቀኝ በኩል ወደ መስመር ከተጠጋ ቦታ ከወንድማገኝ ማዕረግ ጋር ታግሎ በቀጥታ ለማሻማት በሚመስል መልኩ ወደ ውስጥ ያሻገራት ኳስ የሰይድ ሀብታሙ የቦታ አጠባበቅ ስህተት ታክሎበት መረቡ ላይ ኳሷ አርፋለች። በቀሩት የጨዋታ ደቂቃዎች የተለየ ነገርን ሳያስመለክተን በጣናው ሞገድ 1ለ0 ድል አድራጊነት ተቋጭቷል።