መረጃዎች| 51ኛ የጨዋታ ቀን

በ13ኛ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት የሚካሄዱ መርሀ-ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል።

መቐለ 70 እንደርታ ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ

ድልን አጥብቀው የሚሹ በወራጅ ቀጠናው ውስጥ የሚገኙ ክለቦች የሚያገናኘው ‘የትግራይ ደርቢ’ ተብሎ የሚጠራው ጨዋታ ከዚህ ቀደም በሊጉ ተጠባቂ ከነበሩና በድራማዊ ክስተቶች ታጅበው ከሚካሄዱ የሀገሪቱ ደርቢዎች አንዱ ነበር። የነገው ጨዋታም ምንም እንኳን በእንደ ከዚህ ቀደም ሁኔታ ይካሄዳል ተብሎ ባይገመትም በሁለቱም ክለቦች ካለው የድል ረሀብ መነሻነት ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።

በአስራ አንድ ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሚያደርጉት ጉዞ በአንድ ነጥብ በሊጉ ግርጌ የሚገኘውን ወልዋሎ ማሸነፍ ግድ ይላቸዋል።

ከድል ጋር ከተፋታ ስድስት የጨዋታ ሳምንታትን ያሳለፈው መቐለ ከነገው ፍልሚያ የሚገኘው ነጥብ እጅግ አስፈላጊው ነው። በመጨረሻው መርሀ-ግብር ከሽንፈት አገግሞ ነጥብ ተጋርቶ የወጣው ቡድኑ ምንም እንኳን በሊጉ በርከት ያሉ ግቦች በማስተናገድ በሦስተኛ ደረጃነት ቢቀመጥም
በቅርብ ሳምንታት ለክፉ የማይሰጥ የመከላከል አደረጃጀት ገንብቷል፤ ሆኖም ጉልህ የግብ ማስቆጠር ችግር ይስተዋልበታል። ኳስና መረብ ካገናኘ ሦስት የጨዋታ ሳምንታት ያስቆጠረው ቡድኑ የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ያሬድ ብርሀኑን ጨምሮ በርከት ያሉ ተሰላፊዎቹ በጉዳት እና በቅጣት ማጣቱ ስብስቡን ክፉኛ ጎድቶታል።
ይህን ተከትሎም የመልሶ ማጥቃት አጨዋወቱ እንደ ቀደሙት የመጀመርያ ሳምንታት ስል መሆን አቅቶታል።

ምዓም አናብስቱ ከድል አልባው የሳምንታት ጉዞ ለመላቀቅ እና በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ ላይ ከፍ ለማለት ከዚህ ጨዋታ ካልጀመሩ ቀጣይ መንገዳቸው መክበዱ የሚቀር አይመስልም።

አስከፊ የውድድር ዓመቱን መቀልበስ የተሳነው ወልዋሎ ነገም የተስፋ ጭላንጭልን ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባል።

እስካሁን አንድ ነጥብ ብቻ ያሳኩት ቢጫዎቹ ብያንስ ከወራጅ ቀጣናው ካሉ ሌሎች ክለቦች ያላቸውን የነጥብ ልዩነት በማጥበብ የተሻለ ተስፋ ለመያዝ የድሬ ቆይታቸውን መጥፎ ትዝታ አዳማ ላይ በመርሳት በፍጥነት ወደ ውጤት መመለስ ያስፈልጋቸዋል። በውድድር ዓመቱ ዝቅተኛ የግብ መጠን(2) በማስቆጠር እና በርከት ያሉ ግቦች ማስተናገድ (16) የቻሉት ቢጫዎቹ ካሉበት የውጤት አዘቅት ለመውጣት ሁለንተናዊ ለውጥ ማድረግ ግድ ይላቸዋል። በተለይም በጨዋታ በአማካይ 1.6 ግቦች ያስተናገደ የመከላከል አደረጃጀታቸው አፋጣኝ መፍትሔ የሚፈልግ የቡድኑ ዋነኛ ችግር ነው።

በመቐለ 70 እንደርታዎች በኩል አምበሉ ያሬድ ከበደ በቅጣት፤ ያብስራ ተስፋዬ፣ ያሬድ ብርሀኑ፣ መናፍ ዐወል፣ ዮናስ ግርማይ፣ ኪሩቤል ኃይሉ፣ አሸናፊ ሀፍቱ እና አማኑኤል ልዑል ደግሞ በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም። በወልዋሎ በኩልም ዳዋ ሆቴሳ፣ ሰለሞን ገመች እና አላዛር ሽመልስ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም።

ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ አራት ጊዜ ተገናኝተው ሁለት ጊዜ አቻ ሲለያዩ መቐለ አንድ፣ ወልዋሎ አንድ ጊዜ ድል አስመዝግበዋል። ቀይ ለባሾቹ 3፣ ቢጫ ለባሾቹ ደግሞ 2 ጎል አስቆጥረዋል። (በመቐለ 70 እንደርታ አንድ ለባዶ አሸናፊነት የተጠናቀቀው የ2012 ውድድር ዓመት ጨዋታ አልተካተተም)።

አዳማ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ተጋጣሚያቻቸውን አሸንፈው ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርቡት እና ተመሳሳይ ነጥብ ያስመዘገቡ ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ወልዋሎን በማሸነፍ የከተማቸን ቆይታ አሐዱ ያሉት አዳማ ከተማዎች በነገው ዕለት የቅርብ ተፎካካሪያቸውን ማሸነፍ ከቻሉ በደረጃ ሰንጠረዡ ከፍ የማለት ዕድል አላቸው።

በውድድር ዓመቱ አስራ አራት ግቦች በማስቆጠር ጥሩ የፊት መስመር ጥምረት የገነቡት አዳማዎች በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ካስቆጠሩባቸው መርሀ-ግብሮች መልስ ውጤታማው የፊት መስመር ጥንካሬያቸው ማስቀጠል ቀዳሚ ስራቸው መሆን ይኖርበታል። አዳማ ከተማ በጨዋታ በአማካይ 1.2 ግቦች ማስቆጠር ቢችልም አስራ አራት ግቦች ያስተናገደው የኋላ ክፍሉ ድክመት ቡድኑ ወደ ፊት እንዳይራመድ እክል ሆኖበታል። ምንም እንኳን በመጨረሻው መርሀ-ግብር ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ መረቡን ሳያስደፍር መውጣት ቢችልም በነገው ዕለት ጠንካራ የማጥቃት አጨዋወት ያለው ቡድን እንደመግጠሙ የመከላከል አደረጃጀቱ ይበልጥ ማጠናከር ይኖርበታል።

በአስራ አምስት ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በደረጃ ሰንጠረዡ ሽቅብ ለመውጣት ከነገው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

ከሦስት ድል አልባ ጨዋታዎች መልስ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በማሸነፍ መጠነኛ እፎይታ ያገኙት ፈረሰኞቹ ለሳምንታት ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸው ወደ ውጤት ለመመንዘር ተቸግረው ቢቆዩም በመጨረሻው ሳምንት ወደ ድል ተመልሰዋል። ቡድኑ በመጨረሻው ሳምንት ወደ ድል ከመመለሱም ባለፈ ከዚህ ቀደም ዋነኛ የቡድኑ ችግር የነበረው የአፈፃፀም ድክመት ተስፋ ሰጪ መሻሻሎች ያሳየበት ነበር፤ ቡድኑ ብልጫ ወስዶ በተጫወተባቸው ከባህርዳር ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጋር በተከናወኑ ጨዋታዎች በተጠቀሰው ችግር ነጥቦ ተጋርቶ መውጣቱ ይታወሳል። በነገው ጨዋታም በመጨረሻው ሳምንት የነበረው ጥንካሬ ለማስቀጠል ተመሳሳይ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በአዳማ ከተማ በኩል ቢኒያም ዐይተን እና ዳግም ተፈራ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩልም ፍፁም ጥላሁን በአምስት ቢጫ ምክንያት በቅጣት የማይኖር ሲሆን በትከሻ ጉዳት የመጨረሻ ልምምድ ላይ ያልተሳተፈው አማኑኤል ተርፉም ግልጋሎት መስጠቱ አጠራጣሪ ነው። በክረምቱ ቡድኑን የተቀላቀለው ዩጋንዳዊው ተከላካይ ጊፍት ፍሬድ አሁንም በጉዳት ከቡድኑ ስብስብ ውጪ ነው።

ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 44 ጊዜ ተገናኝተዋል። በጨዋታዎቹ 23 ጊዜ ድል ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ 59 ግቦችን ሲያስቆጥር 8 ጨዋታዎችን በድል የተወጣው አዳማ ከተማ ደግሞ 32 ግቦችን አስቆጥሯል። ክለቦቹ 13 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።