ሪፖርት | ምዓም አናብስቶቹ ከናፈቃቸው ድል ጋር ታርቀዋል

በተጠባቂው ጨዋታ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አዎት ኪዳኔ ምዓም አናብስቶቹ ከቢጫዎቹ ወሳኝ ሦስት ነጥቦችን እንዲወስዱ አስችሏል።

ምዓም አናብስቶቹ በ12ኛው ሳምንት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አቻ ከተለያየበት ቋሚ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ ሲያደርጉ በዚህም ብሩክ ሙሉጌታን በክብሮም አፅብሃ ቀይረው ሲቀርቡ በአንፃሩ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲዎች ደግሞ በአዳማ ከተማ ከተረታው የመጀመሪያ አስራ አንድ ውስጥ ሦስት ለውጦችን ሲያደርጉ ታዬ ጋሻው ፤ ሰለሞን ገመቹ እና ዳዋ ሆጤሳን በማሳረፍ ሱልጣን በርሄ ፤ ዳዊት ገብሩ እና ናትናኤል ሰለሞንን ተክተው ቀርበዋል።

ቀዝቀዝ ባለ ጨዋታ እንቅስቃሴ የጀመረው የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች መረጋጋት ተስኗቸው ያልተሳኩ የኳስ ቅብብል ሲያደርጉ የተስተዋሉበት ነበር።

ቢጫ ለባሾቹ በረጃጅም እንዲሁም ምዓም አናብስቶች ደግሞ በአጫጭር የኳስ ቅብብሎች ለመጫወት ሲጥሩ ባስተዋልንበት ጨዋታ በ12ኛው ደቂቃ ላይ መቐለ 70 እንደርታ ከማዕዘን ሞት በተሻማ ኳስ ግብ ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጭ በሚል ሲሻርባቸው በ
ወልዋሎዎች ደግሞ በ14ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ሰለሞን በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው እና ሶፎንያስ ሰይፈ የመለሰበት ሙከራ የአጋማሹ ጠንካራና ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር።

በ23ኛው ደቂቃ ሰለሞን ሀብቴ ቀጥታ ወደ ግብ መጥቶ የቢጫ ለባሾቹ የግብ ዘብ በግሩም ሁኔታ ያዳነበት ሌላው በአጋማሹ የተመለከትነው ጥሩ ሙከራ ነበር።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ጨዋታው ግለቱን ጨምሮ በጠንካራ ፉክክር ሲመለስ ቡድኖቹ ከመጀመሪያ አጋማሽ በተሻለ እንቅስቃሴ ተመልሰው እየተፈራረቁ ብልጫ ወስደዋል። በ56ኛው ደቂቃ ላይ ሱልጣን በርሄ በቀኝ ማዕዘን ምት ቦታ አከባቢ ያሻገረውን ኳስ ናትናኤል ሰለሞን ብቻውን ሆኖ አግኝቶ እንዲሁም በ64ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ናትናኤል ሰለሞን ከሶፎንያስ ሰይፈ ጋር ተገናኝቶ ያመከናት ኳስ ቢጫ ለባሾቹን ቀዳሚ ለማድረግ የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

በኳስ ንክኪ ብልጫ የነበራቸው ምዓም አናብስቶች በ82ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የጥረታቸው ውጤት የሆነችዋን ግብ ተቀይሮ በገባው በአዎት ኪዳኔ አማካኝነት መረብ ላይ አሳርፈዋል። ክብሮም አፀብሃ በቀኝ መስመር ሳጥን ውስጥ ሆኖ ያሻገረውን ኳስ አዎት ኪዳኔ አግንቶ በቀላሉ ወደግብነት ቀይሯታል።


ግብ ካስቆጠሩ በኋላም ምዓም አናብስቶቹ የናፈቃቸውን ድል ለማስጠበቅ በመከላከል የተጫወቱ ሲሆን ቢጫ ለባሾቹ በአንፃሩ ሚያገኙትን ኳሶች ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመጣል ጫናን ፈጥረው ቢጫወቱም ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል ፤ ተጠባቂው ጨዋታ በምዓም አናብቶቹ የበላይነት ተደምድሟል።