ዳሸን ባንክ እና ኖቫ ኮኔክሽንስ የሦስት ዓመታት የስፖንሰርሺፕ ስምምነት በዛሬው ዕለት በዳሸን ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ተፈራረሙ፡፡
በሀገረ አሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ መቀመጫውን ያደረገው ኖቫ ኮኔክሽንስ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያሳትፈውን ግራንድ አፍሪካን ረን እንዲሁም ለሀገር ባለውለታ የሰሩ ሰዎችን የሚያወድሰውን ኢምፓክት አዋርድ ሁነቶች እንደሚያዘጋጅ ይታወቃል። ሁነቶቹ ባለፉት ስድስት ዓመታት በተከታታይ ሲደረጉ አጋር የነበረው ዳሽን ባንክ በዛሬው ዕለት ውሉን ማደሱን ይፋ አድርጓል።
ዳሸን ባንክን በመወከል ስምምነቱን የተፈራረሙት የባንኩ ቺፍ ስትራቴጂ ኦፊሰር አቶ ኤልያስ ሁሴን እንደተናገሩት ዳሸን ባንክ ኖቫ ኮኔክሽንስ የሚያዘጋጃቸው የእነዚህ መርሃ-ግብሮች አጋር መሆኑን በሰሜን አሜሪካ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጋር ያለውን ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክር አመላክተዋል፡፡
የኖቫ ኮኔክሽንስ ዳይሬክተር ዶ/ር ጋሻው አበዛ በበኩላቸው ዳሸን ባንክ ኖቫ ኮኔክሽንስ ባለፉት አራት ዓመታት ባዘጋጃቸው መርሃ-ግብሮች አጋር ሆኖ በመቆየቱና ይህን አጋርነቱንም በቀጣይ ሶስት ዓመታት ለማስቀጠል ፈቃደኛ በመሆኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ስምምነቱ ዳሸን ባንክ ከኖቫ ኮኔክሽንስ ጋር በመተባበር በቀጣይ ሶስት ዓመታት በአሜሪካ ዋሺንግተን ከተማ ታላቁን የአፍሪካ ሩጫ ስኬታማ በሆነ መልኩ ለማካሄድ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ለሆኑ ኢትዮጵያዊያን በየአመቱ ዕዉቅና ለመስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል።
ስምምነቱ የተለያዩ የዳሸን ባንክ አገልግሎቶች በሰሜን አሜሪካ ለሚገኘው የዳያስፖራ ማህበረሰብ ዘንድ ይበልጥ ተደራሽ የሚሆኑበትን ዕድል እንደሚፈጥርና ዳሸን ባንክ ማኅበረሰቡ የሚሰባሰብባቸውን መርሃ-ግብሮች መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያሳየበት መሆኑ ከመድረኩ ተነስቷል፡፡