መረጃዎች | 52ኛ የጨዋታ ቀን

በ13ኛ ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ዕለት የሚከናወኑ መርሐግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ስሑል ሽረ ከ መቻል

በደረጃ ሰንጠረዡ በተለያየ ፅንፍ የሚገኙት ስሑል ሽረ እና መቻል የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነው።

በአስራ አንድ ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ስሑል ሽረዎች በመጨረሻው ሳምንት በኢትዮጵያ መድን ከደረሰባቸው ሽንፈት አገግመው ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ከመቻል ጋር ይፋለማሉ።

በመጨረሻው ጨዋታ በሁሉም ረገድ ደካማ እንቅስቃሴ በማድረግ ሽንፈት ያስተናገደው ቡድኑ  በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሁለት ግብ በላይ ተቆጥሮበታል። ቡድኑ ከሽንፈቱ በፊት በተከናወኑ ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ ግቡን ሳያስደፍር በመውጣት አንድ ግብ ብቻ ማስተናገድ ቢችልም ደካማ የመከላከል ብቃት ባሳየበት ጨዋታ ሦስት ግቦች ማስተናገዱን ተከትሎ በውድድር ዓመቱ ያስተናገዳቸው ግቦች አስራ ሁለት ደርሰዋል።

ስሑል ሽረዎች በጨዋታው በቅርብ ሳምንታት ከነበራቸው የማጥቃት አቅም አንፃር ሲታይ በመጠኑ መሻሻል ማሳየታቸው አይካድም፤ በሁለቱም አጋማሾች የፈጠሯቸው ሁለት ንፁህ የግብ ዕድሎችም የዚህ ማሳያ ናቸው። ሆኖም ለሁለት የጨዋታ ሳምንታት መረቡን ሳያስደፍር ቢወጣም ዓመቱን በጀመረበት ጥንካሬው ላይ የማይገኘው የመከላከል አደረጃጀታቸው አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚፈልግ ተስተውሏል። በነገው ዕለትም በሊጉ ከፍተኛ የግብ መጠን በማስቆጠር ቀዳሚ የሆነ ቡድን እንደመግጠማቸው የባለፈው ሳምንት ድክመታቸውን ቀርፈው መቅረብ ግድ ይላቸዋል።

ከዘጠኝ ጨዋታዎች በኋላ ሽንፈት የቀመሰው መቻል በ21 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ለሳምንታት በሊጉ አናት ላይ ተቀምጦ የነበረው ቡድኑ ዳግም ወደ መሪነቱ ለመመለስም በነገው ጨዋታ ድል ማድረግ አስፈላጊው ነው።

ጦሩ በተከታታይ ሁለት ሳምንታት ነጥብ መጣሉን ተከትሎ መሪነቱን ለማስረከብ ተገዷል። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው ስድስት ነጥብ አንዱን ብቻ ያሳካው ቡድኑ ከውጤቱም ባሻገር ኳስና መረብ ካገናኘ 180 ደቂቃዎች ተቆጥረዋል። መሰል ተከታታይ የጎል ድርቅ በሊጉ የተለመደ ቢሆንም ቡድኑ በተከታታይ ዘጠኝ መርሐግብሮች ላይ በጨዋታ በአማካይ 2.1 ግቦች ያስቆጠረ ጠንካራ የፊት መስመር ጥምረት ያለው ቡድን እንደመሆኑ  ለዋንጫ በሚያደርገው ጉዞ መሰል ችግሮችን በቶሎ መቅረፍ ይጠበቅበታል።

በስሑል ሽረ በኩል ጥዑመልሳን ኃይለሚካኤል እና አዲስ ግርማ በጉዳት ኬቨን አርጊዲ ደግሞ በሕመም ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው።
የመቻልን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ስሑል ሽረ አንድ ጨዋታ ድል ሲያደርግ አንድ ጨዋታ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር። በግንኙነቱ ስሑል ሽረ አራት መቻል ደግሞ ሦስት ግቦችን አስቆጥረዋል።

ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ከሳምንታት በኋላ ያገኙትን ድል ለማስጠበቅ ወደ ሜዳ የሚገቡት ሲዳማ ቡናዎች እና ድልን አጥብቀው የሚፈልጉትን ንግድ ባንኮችን የሚያገናኘው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።

ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች መልስ አርባምንጭ ከተማን አንድ ለባዶ በማሸነፍ ያንሠራሩት ሲዳማ ቡናዎች ተከታታይ ድል አስመዝግበው ደረጃቸውን ለማሻሻል እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን ድል አድርገው ስኬታማ አጀማመር ማድረግ ችለው የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ከአምስተኛው ሳምንት በኋላ ነገሮች በጥሩ መንገድ አልሄዱላቸውም። ቡድኑ ከተጠቀሰው የጨዋታ ሳምንት በኋላ እየተዳከመ ሄዶ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ በማሳካት ፈታኝ ሳምንታት አሳልፏል። በመጨረሻው ሳምንት ግን ከተከታታይ ሽንፈቶች መልስ ውድ ሦስት ነጥብ ከማስመዝገቡም በተጨማሪ በሦስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ካስተናገደ በኋላ መረቡን ሳያስደፍር ወጥቷል። ቡድኑ የግለሰባዊ ስህተቶች ዋጋ ካስከፈሉት የድሬዳዋ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ መልስ በመከላከል አደረጃጀቱ መጠነኛ መሻሻል ማሳየቱም በጉልህ ተስተውሏል።

አስር ጨዋታዎችን አከናውነው አስር ነጥብ የሰበሰቡት ንግድ ባንኮች 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በ10 ሳምንታት የሊጉ ቆይታ ሁለት ድል፣ አራት የአቻ እና አራት ሽንፈት ያስተናገዱት ባንኮች ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በድምሩ ከሦስት ነጥብ በላይ  ማግኘት ተስኗቸው አደገኛው ቀጠና ላይ ተቀምጠዋል። እርግጥ ቡድኑ ከብዙዎች ግምት ውጭ በመጥፎ የውጤት ጎዳና እየተጓዘ ቢገኝም በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ግን ብዙ ለትችት የሚዳርገው ብቃት አያሳይም። በዋናነት ግን ባለፉት አራት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት የተሳነው የማጥቃት አጨዋወታቸው የቡድኑ ዋነኛ ደካማ ጎን ነው።

ቡድኑ መረቡን ሳያስደፍር መውጣት በተሳነበት የመጀመሪዎቹ ሰባት የጨዋታ ሳምንታት  አስራ አንድ ግቦች በማስተናገድ ደካማ ቁጥሮች ማስመዝገብ ቢችልም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ግን አንድ ግብ ብቻ በማስተናገድ የመከላከል ችግሩን ፈትቷል። በነገው ዕለት ከአምስት የሊግ ጨዋታዎች በኃላ ወደ ድል ለመመለስ ግን ጉልህ የግብ ማስቆጠር ችግሩን መፍታት ይጠበቅበታል።

በሲዳማ ቡና በኩል ከብርሃኑ በቀለ ቅጣት ውጪ ሁሉም የቡድን አባላቶች ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በንግድ ባንክ በኩል ደግሞ ረዘም ላሉ ጊዜያት ከሜዳ እንደሚርቁ የሚጠበቁት ፉዓድ ፈረጃ እና ሱሌይማን ሀሚድ አሁንም ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ ለቡድኑ እንደ መልካም ዜና የሚቆጠረው አምበሉ ፈቱዲን ጀማል ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ሜዳ የሚመለስ መሆኑ ሲሆን የተቀሩት የቡድኑ አባላት ከቅጣት እና ከጉዳት ነፃ ሆነው የነገውን ጨዋታ የሚጠባበቁ ይሆናል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ18 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን አመዛኙ 10 ጨዋታ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነው። ሲዳማ 5 ጨዋታ ሲያሸንፍ ንግድ ባንክ ደግሞ 3 አሸንፏል። በግንኙነታቸው ንግድ ባንክ 21፣ ሲዳማ ቡና ደግሞ 20 ግቦችን አስቆጥረዋል።