ዘንድሮ ቡድኑን የተቀላቀለው ጋናዊው የመሀል ተከላካይ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር መለያየቱ ታውቋል።
በአሰልጣኝ በረከት ደሙ እየተመራ ዳግም ወደ ሊጉ የተመለሰው አርባምንጭ ከተማ ዘንድሮ ወደ ቡድኑ ከተቀላቀሉ ተጫዋቾች መካከል ባሳለፍነው ዓመት በመቻል ቤት ጥሩ የሚባል ጊዜን አሳልፎ የነበረው ጋናዊው ተከላካይ ስቴፈን ባዱ አኖርኬን አንዱ ነበር።
ሆኖም ጋናዊው ተከላካይ የመጀመርያዎቹ ሳምንታት ለቡድኑ ግልጋሎት እየሰጠ የነበረ ቢሆንም ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ያለፉትን ሳምንታት ከሜዳ መራቁ ይታወሳል።
በአዲስ አበባ ህክምናውን እየተከታተለ የቆየው ስቴፈን ከጉዳቱ ክብደት አንፃር ዳግም ወደ ሜዳ ለመመለስ የስድስት ወር ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ እና ወደ ሀገሩ በመሄድ ህክምናውን መከታተል ስለፈለገ ከክለቡ ጋር ያለውን ውል በመቅደድ በስምምነት ለመለያየት መቻሉን ከክለቡ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።
አርባምንጭ ከተማ እስካሁን ካደረጋቸው አስራ አንድ ጨዋታዎች አስራ ሦስት ነጥብ በመሰብሰብ በሊጉ አስራ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።