ሪፖርት| ኢትዮጵያ መድን ወደ መሪዎቹ የተጠጋበትን ወሳኝ ድል አስመዝግቧል

ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ባቀበለበት ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ወላይታ ድቻን አሸንፏል።

ወላይታ ድቻዎች ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው ቋሚ አሰላለፍ ፍፁም ግርማ፣ ኬኔዲ ከበደ፣ አብነት ደምሴ፣ ብስራት በቀለ እና ባዬ ገዛኸኝ በተስፋዬ መላኩ፣ ምንተስኖት ተስፋዬ፣ ሙሉቀን አዲሱ፣ መሳይ ሰለሞን እና ካርሎስ ዳምጠው ተክተው ሲገቡ ኢትዮጵያ መድኖችም ስሑል ሽረን ካሸነፈው ቋሚ ረመዳን ሁሴን እና ጋቶች ፓኖም በዳዊት ተፈራ እና ዋንጫ ቱት ተክተው ገብተዋል።


በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ፣ ተደጋጋሚ ጥፋቶች እና ጉሽምያዎች ታጅቦ በተካሄደው የመጀመርያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በተለያየ አቀራረብ ለማጥቃት የሞከሩበት ቢሆንም በሙከራዎች የታጀበ አልነበረም። ጨዋታው በተጀመረ 15ኛው ደቂቃም በጥሩ መንፈስ ጨዋታውን የጀመሩት የጦና ንቦቹ መሪ የምታደርጋቸውን ግብ ማስቆጠር ችለዋል፤ ያሬድ ዳርዛ ከሳጥኑ የግራ ክፍል በድንቅ ክህሎት አታሎ ወደ ሳጥን አሻግሯት ብዙአየሁ ሰይፉ ከመረቡ ጋር ያዋሀዳት ኳስም ወላይታ ድቻን መሪ አድርጋለች።

ከግቧ በኋላ መድኖች በርከት ያሉ ወደ ሙከራነት ያልተቀየሩ የግብ ዕድሎች ፈጥረው ሳይጠቀሙበት ከቀሩ በኋላ በ32ኛው ደቂቃ ላይ በሚልዮን ሰለሞን አማካኝነት የአቻነቷን ግብ አስቆጥረዋል፤ ወገኔ ገዛኸኝ ከመዓዘን ምት አሻግሯት ተከላካዩ ሚልዮን ሰለሞን በግሩም ሁኔታ በግንባር ያስቆጠራት ኳስም መድንን ወደ ጨዋታው የመለሰች ግብ ነበረች።

ከአቻነት ግቧ በኋላ የተሻለ የማጥቃት አቅም የነበራቸው መድኖች ወገኔ ገዛኸኝ አሻምቷት መሐመድ አበራ በግንባር ባደረጋት ሙከራ እና ሚልዮን ሰለሞን ከመሀል ሜዳ እየገፋ አክርሮ መቷት አብነት ይስሀቅ በድንቅ ብቃት ባወጣት ወርቃማ ሙከራ ጨዋታውን ለመምራት ተቃርበው ነበር።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት አጋማሽ ኢትዮጵያ መድን ብልጫ የወሰደበት ነበር። የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድም ሆነ ሙከራዎች በማድረግ የተሻለ የነበረው ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ ዳዊት ተፈራ አሻምቷቸው በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ባደረገው ሚልዮን ሰለሞን ያደረጋቸው ሁለት ሙከራዎች እንዲሁም አለን ካይዋ ከዳዊት ተፈራ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ባደረጋት ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። በ84ኛው ደቂቃም ጥረታቸው ሰምሮ ጨዋታውን መምራት ችለዋል፤ መሐመድ አበራ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ በረዥሙ የለጋትን ኳስ ተጠቅሞ ያስቆጠራት ግብም መድንን የማታ ማታ አሸናፊ ያደረገች ግብ ነበረች።


በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ የመከላከል ቅርፅ ቢኖራቸውም በርከት ያሉ የጠሩ ግብ ዕድሎች መፍጠር ያልቻሉት የጦና ንቦቹም ካርሎስ ዳምጠው በሳጥኑ ውስጥ ሆኖ አግኝቷት ወደ ግብነት ባልቀየራት ኳስ እና ያሬድ ዳርዛ በመጨረሻው ደቂቃ ባደረጋት ድንቅ ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ብያደርጉም ጨዋታው በመድን የሁለት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል ፤ ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ መድን ደረጃው ወደ 4ኛ ከፍ ማድረግ ችሏል።