ትውልደ ኢትዮጵያዊው ጦሩን ተቀላቅሏል

በአዲስ አበባ የተወለደው የተከላካይ አማካይ ዳግም የመከላከያ ሰራዊቱን ለማገልገል ዘምቷል።


በኢስራኤሉ ክለብ ሀፖል ሀደራ የሚጫወተው ትውልደ ኢትዮጵያዊው አማካይ መናሸ ዘለቀ ዳግም የኢስራኤል ጦር ተቀላቅሏል።

ከአንድ ዓመት በፊትም በተመሳሳይ ከክለቡ ተለይቶ የተጠባባቂ ጦሩን በመቀላቀል በጋዛ እና ሊባኖን ለ115 ቀናት ጦሩን ያገለገለው ይህ የተከላካይ አማካይ ከጦር ሜዳ መልስ ክለቡን ተቀላቅሎ በአስራ አራት ጨዋታዎች ቡድኑን አገልግሏል። በአዲስ አበባ የተወለደው የሰላሣ አራት ዓመቱ መናሸ በዚህ ሳምንት ቡድኑ በሀፖይል ቤር ሻቫ ሽንፈት በገጠመው ማግስት ክለቡን ተሰናብቶ ከአንድ ዓመት በኋላ ዳግም ጦሩን ተቀላቅሏል።

በውድድር ዓመቱ መጀመርያ የቤኒ ሳክህኒን ደጋፊዎች ባደረሱበት ጥቃት መነጋገርያ የነበረው ትውልደ ኢትዮጵያዊው በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኘውን የመከላከያ ሠራዊት ጦር ካምፕ ይገኛል።