በ14ኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን የሚከናወኑ ተጠባቂ መርሀ-ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ድልን አጥብቀው የሚሹ የመዲናይቱ ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሀ-ግብር ነው።
በአስራ አንድ ነጥቦች ወራጅ ቀጠናው ውስጥ የሚገኙት ሻምፕዮኖቹ ንግድ ባንኮች ለሳምንታት ከራቃቸው ድል ጋር ለመገናኘት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ይገጥማሉ።
ድል ከተቀዳጀ ስድስት የጨዋታ ሳምንታት ያስቆጠረው ቡድኑ አሁንም ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ማድረጉ ቢቀጥልም ወደ ድል መንገድ መመለስ አልቻለም። በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሀ ግብሮች ተከታታይ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት ሀምራዊ ለባሾቹ በጨዋታው ከአራት ሳምንታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ኳስና መረብ ማገናኘት ችለዋል። በሊጉ በርከት ያሉ ግቦች ካስተናገዱ አምስት ክለቦች ውስጥ የሚገኙት ሻምፕዮኖቹ ከመጨረሻዎቹ አራት መርሀ-ግብሮች በሁለቱ መረባቸውን ሳያስደፍሩ በመውጣት ሁለት ግቦች ብቻ ማስተናገዳቸው በጥሩ ጎኑ የሚነሳላቸው ነጥብ ቢሆንም አሁንም የግብ ማስቆጠር ክፍተታቸው ማረም ይኖርባቸዋል።
ከዘጠኝ ሽንፈት አልባ ሳምንታት በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ያስተናገዱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች
ከነገው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ይዞ መውጣት ብያንስ ሦስት ደረጃዎች እንዲያሻሽሉ ይረዳቸዋል።
ኤሌክትሪኮች በሊጉ ሰባት የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ከሚመራው ፋሲል ከነማ በአንድ ዝቅ ብለው በስድስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተው መውጣት ችለዋል፤ ቡድኑ ለዘጠኝ ሳምንታት ሽንፈት አልባ ጉዞ ማድረግ ቢችልም በስድስቱ ነጥብ ተጋርቶ በመውጣቱ ከደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ እንዲያሽቆለቁል ሆኗል።
በአመዛዡ ቀጥተኛ እንዲሁም በሁለቱም መስመሮች መሰረት ያደረገ የማጥቃት አጨዋወት የሚከተሉት ኤሌክትሪች ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች
የፊት መስመራቸው በሚፈለገው ደረጃ ይገኛል ብሎ መናገር አይቻልም። በተጠቀሱት የመጨረሻ ሦስት መርሀ-ግብሮች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው ቡድኑ አሁንም በቀላሉ ለጥቃት የማይጋለጥ የመከላከል አደረጃጀት ጥንካሬው ማስቀጠል ቢችልም ግብ የማስቆጠር አቅም ማነስ ለተከታታይ አራት ሳምንታት ከድል ጋር አራርቆታል።
በስድስተኛው እና በሰባተኛው ሳምንት በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች በድምሩ አምስት ግቦች በማስቆጠር ተስፋ ሰጪ የፊት መስመር ብቃት ያሳየ አቀራረብ የነበራቸው አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በተጠቀሱት ጨዋታዎቻች ውጤታማ የነበረው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የሚፈጥራቸው ንፁህ የግብ ዕድሎች በቀጣዮቹ ጨዋታዎች መመናመን ቡድኑ በሚፈለገው ደረጃ ግብ እንዳያስቆጥር አድርጎታል። በነገው ጨዋታም በፊት መስመሩ ውስን ለውጦች ማድረግ ከጨዋታው አንዳች ነገር ይዘው እንዲወጡ ያግዛቸዋል ተብሎ ይገመታል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፉአድ ፈረጃ እና ሱሌይማን ሀሚድ አሁንም ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው በነገው ጨዋታ እነርሱን የሚያጣ ሲሆን የተቀሩት የቡድኑ ስብስብ ኢትዮ ኤሌትሪክን ለመፋለም ዝግጁ ናቸው። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል በሁለት ቢጫ ከሜዳ የወጣው ሐብታሙ ሸዋለም በቅጣት የማይኖር ሲሆን ተከላካዮ አብዱላሂ አላዮ አሁንም ከጉዳቱ ባለማገገሙ ለነገው ጨዋታ አይደርስም። ዘንድሮ ቡድኑን ከተቀላቀለ በኋላ በጉዳት የከረመው ገለታ ሀይሉ ወደ ልምምድ መመለሱ ሲሰማ ከዚህ ውጭ ያሉት የቡድኑ ተጫዋቾች ነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸውን አውቀናል።
ሁለቱ ቡድኖች ከ2009 በኋላ በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ የሚገናኙ ቢሆንም ከዚ ቀደም በሊጉ 34 ጊዜ የግንኙነት ታሪክ አላቸው። ኤሌክትሪክ 13 አሸንፎ 51 ጎሎች ስያስቆጥር፤ ባንክ 10 አሸንፎ 42 ጎሎች አስቆጥሯል። በ 11 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ከሳምንት በፊት በኢትዮጵያ ዋንጫ ተገናኝተው ንግድ ባንክ 2-0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
መቻል ከ ድሬዳዋ ከተማ
የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ የሆነው በውድድር ዓመቱ ሁለት ሽንፈቶች ብቻ የገጠማቸው መሪው መቻል እና ድሬዳዋ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይታመናል።
በዘንድሮ የውድድር ዓመት ሁለት ጨዋታ ብቻ ተረቶ
ሀያ አራት ነጥቦች በመሰብሰብ ሊጉን የሚመራው መቻል ሁነኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ ይዘልቃል ተብሎ ከሚገመተው ድሬዳዋ ከተማ በሚያደርገው ጨዋታ ወሳኝ ድል ማስመዝገብን እያለመ ወደ ሜዳ ይገባል።
በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚመራው ቡድኑ ተጋጣሚ ላይ ብዙ ግቦችን (21) በማስቆጠር ከሚጠቀሱ ክለቦች ቀዳሚው ነው።
ለዚህ ጥንካሬ ዋነኛ ተጠቃሽ የሆነው ደግሞ ቡድኑ በበርካታ ማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጨዋቾች የተገነባ እና ብዙ የግብ ምንጮች መያዙ ነው።
በተከታታይ ጨዋታዎች ግቦችን በማስቆጠር የሚገኘው እና ስድስት የሊግ ግቦች ያሉት ሽመልስ በቀለ፤ በአምናው ግብ የማስቆጠር ጥንካሬው ባይገኝም ወደ ኋላ እየተሳበ የግብ ዕድሎች በመፍጠር የሚገኘው ምንይሉ ወንድሙ፤ በረከት ደስታ እና ሌሎች ጥሩ የማጥቃት አበርክቶ ያላቸው ተጫዋቾች የፊት መስመሩን ጥንካሬ አላብሰውታል።
በነገውም ዕለትም እነኚህ የቡድኑ ቁልፍ የማጥቃት መሳርያዎች ከብርቱካናማዎቹ ተከላካዮች የሚያደርጉት ፍጥጫ ጨዋታው ተጠባቂ ያደርገዋል።
በአስራ ስምንት ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ብርቱካናማዎቹ ከሦስት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ከድል ጋር ለመታረቅ የሊጉን መሪ ይገጥማሉ።
ብርቱካናማዎቹ በውድድር ዓመቱ ጥቂት ሽንፈት ካስተናገዱ የሊጉ ቡድኖች ይጠቀሳሉ፤ ቡድኑ በሊጉ ሁለት ሽንፈቶች ብቻ ከማስተናገዱም በተጨማሪ በመጨረሻዎቹ ስድስት መርሀ-ግብሮች ሽንፈት ሳይቀምስ ቢዘልቅም በርከት ያሉ የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር በጋራ በሁለተኛ ደረጃነት ተቀምጧል። በነገው ዕለትም ከሦስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ ድል መንገድ መመለስ ካልቻለ በሰንጠረዡ ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር የደረጃ ማሽቆልቆል ሊገጥመው የሚችልበት ዕድል የሰፋ ነው።
የብርቱካናማዎቹ የፊት መስመር በርከት ያሉ ግቦች በማስቆጠር ቀዳሚ ከሆኑ ክለቦች አንዱ ቢሆንም ከቅርብ ሳምንታት በቀደመ ጥንካሬው ላይ አይገኝም፤ በመጨረሻዎቹ ሦስት መርሀ-ግብሮች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠር የቻለው ቡድኑ ለወቅታዊው የግብ ማስቆጠር ችግሩ መፍትሄዎችን ይዞ መቅረብ ግድ ይለዋል።
በመቻል በኩል ጉዳት ላይ የነበረው ነስረዲን ኃይሉ ለነገው ጨዋታ እንደሚደርስ ሲታወቅ ዮዳሄ ዳዊት ግን ቀለል ያለ ልምምድ ቢጀምርም ለነገው ጨዋታ አይደርስም። በሌላ ዜና ለረጅም ጊዜያት ጉዳት ላይ የነበረው ተሾመ በላቸው በቅርብ ሳምንታት ወደ ጨዋታ እንደሚመለስ ተሰምቷል። በድሬዳዋ ከተማ በኩልም ያሬድ ታደሰ እና መሐመድኑር ናስር በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም፤ ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳሁን ግን ከቅጣት ተመልሶ ቡድኑን ለማገልገል ዝግጁ ሆኗል።
በሊጉ ከዚህ ቀደም ሀያ ሁለት ጊዜያት የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች መቻሎች በአስራ ሁለት አጋጣሚ ማሸነፍ ሲችሉ በአንፃሩ ድሬዳዎች ደግሞ ሦስት ጨዋታዎች እንዲሁም የተቀሩት ሰባት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።