የአዲስ ግደይ አስደናቂ የቅጣት ምት ጎል ንግድ ባንኮች ከስድስት የጨዋታ ሳምንት በኋላ ከድል ጋር እንዲታረቁ አድርጋለች።
ከሲዳማ ቡና ጋር አንድ አቻ የወጡት ንግድ ባንኮች በዛሬው ጨዋታቸው ከስብስባቸው የአራት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ እንዳለ ዮሐንስ፣ ተመስገን ተስፋዬ፣ ቢንያም ካሳሁን ኪቲካ ጅማን አስቀምጠው በምትኩ ካሌብ አማንክዋህ ተስፋዬ ታምራት፣ ዮናስ ለገሰ እና ቢንያም ጌታቸውን በማስገባት ከውጤት ረሀባቸው ለመላቀቅ ወደ ሜዳ ገብተዋል። እንዲሁም ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በቅዱስ ጊዮርጊስ ካጋጠማቸው ሽንፈት መልስ ስብስባቸው ውስጥ ስድስት ተጫዋቾች በመለወጥ አሸናፊ ጥሩነህ ጌቱ ባፋ፣ ሐብታሙ ሸዋለም፣ አባይነህ ፌኖ፣ እዮብ ገብረማርያም፣ አብዱላዚዝ አማን አሳርፈው ዲንክ ኪያር፣ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ፣ አበባየሁ ዮሐንስ፣ ሄኖክ ገብረህይወት፣ በጋሻው ክንዴ እና አቤል ሐብታሙን ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ፌደራል ዋና ዳኛ አዳነ ወርቁ በመሩት የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ ሁለቱም ከውጤት እንደመራቃቸው እንቅስቃሴያቸው ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት መምረጣቸው ጨዋታ ብዙም ሳቢ አልነበረም በጎል ሙከራ ረገድም ሳይመን ፒተር ሳይታሰብ ከሜዳው ቀኝ ጠርዝ ከርቀት መቶት ግብጠባቂው እና የግቡ አግዳሚ ተጋግዘው ለጥቂት የወጣበት የ9ኛው ደቂቃ ሙከራ ነበር።
በሁለቱም በኩል ወደፊት ለመሄድ የሚያደርጉት ጥረት ኳሶቻቸው እየተቆራረጡ አደጋ መፍጠር ተስኗቸው ጨዋታው በቀጠለበት ሂደት አስደናቂ የቅጣት ምት ጎል በ23ኛው ደቂቃ ንግድ ባንኮች አስቆጥረዋል። አዲስ ግደይ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ከጎሉ ፊት ለፊት በግምት ከሃያ ሜትር ርቀት አዲስ ግደይ በሚታወቅበት መንገድ በግሩም ሁኔታ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎት ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ጎሉ መቆጠር በኋላ ጨዋታው ወደ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ተቀይሮ ኳሶች ወደፊት ቢደርሱም ይህ ነው የሚባል የጎል ሙከራ ለመመልከት ሳንችል ቀርተናል። በተለይ ንግድ ባንኮች የመሐል ሜዳ ክፍሉ ተቆጣጥረው ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ስንመለከት በአንፃሩ ኢትዮ ኤሌትሪኮች ብልጫ በተወሰደባቸው የሜዳ ክፍል ምክንያት ለአጥቂዎቻቸው ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ አቅርቦት ባለመኖሩ በመጀመርያው አጋማሽ አንድም ተጠቃሽ የሆነ የጠራ የግብ ዕል ሳይፈጥሩ አጋማሹ ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ በተሻለ ሁኔታ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ወደ ጨዋታው ለመግባት የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም በመጀመርያው አጋማሽ የነበረባቸውን የጎል ዕድል የመፍጠር ችግር አሁንም መቅረፍ ሳይችሉ ቀርተዋል። አሰልጣኝ በፀሎት አጥቂው ቢንያም ጌታቸውን በመቀየር የተከላካይ አማካይ ቢንያም ካሳሁንን በማስገባት መከላከልን ምርጫቸው አድርገው በመልሶ ማጥቃት በ62ኛው ደቂቃ ኤፍረም ታምሩ ያቀበለውን ሳይመን ፒተር ኢላማውን ሳይጠብቅ የወጣበት ዕድል ተጠቃሽ ካልሆነ በቀር ጨዋታ በሙከራ ረገድ ድርቅ የመታው ነበር።
ጥንቃቄን አጨዋወት ከማጥቃት አማራጭ ጋር ይዘው የተጫዋች ቅያሪ ማድረጋቸውን የቀጠሉት ንግድ ባንኮች በ68ኛው እና 69ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይረው የገቡት አጥቂዎቹ ኪቲካ ጅማ እና ሀይከን ደባሞ ጎል ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ይልቁንም የኪቲካ ጅማ እጅግ የቀረበ ሙከራ ግብጠባቂው እንዲሪስ አብዱለካሂ ባያድንበት ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል መሆን የሚችል ነበር።
በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ጨና ፈጥረው ለመጫወት ያሰቡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ በሁለተኛው አጋማሽም አንድ ተጠቃሽ የጎል ዕድል ሳይፈጥሩ ቀርተዋል። 92ኛው ደቂቃ የንግድ ባንኩ ዮናስ ለገሰ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱን ተከትሎ የበለጠ ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደ ኋላ አፈግፍገው መከላከላቸው ተሳክቶላቸው 1-0 በማሸነፍ ከድል ጋር የታረቁበትን ውጤት አስመዝግበዋል።