በምሽቱ መርሃግብር ብርቱካናማዎቹ ከወቅቱ የሊጉ መሪ ጋር ነጥብ ተጋርተዋል።
መቻሎች በ13ኛው ሳምንት ስሑል ሽረን ከረቱበት ቋሚ አሰላለፋቸው ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ሲቀርቡ ብርቱካናማዎቹ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለግብ ካጠናቀቁበት ጨዋታ ላይ ከተጠቀሙበት ቋሚ 11 ላይ ሶስት ለውጥ ሲያደርጉ በዚህም ድለአዲስ ገብሬ፣ መስዑድ መሐመድ፣ እና ሙኸዲን ሙሳን አሳርፈው በምትካቸው አህመድ ረሺድ ፣አበቡከር ሻሚል እና ተመስገን ደረሰን ተክተው ቀርበዋል።
በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ መሪነት በተጀመረው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ጥንቃቄ መርጠው የጀመሩትም ነበር ፤ የመጀመሪያ የግብ ሙከራም ለመመዝገብ ጨዋታ 11 ደቂቃ ለመጠበቅ ተገደን ነበር።
በ11ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ያደረገውን ጠንካራ ሙከራ የብርቱካናማዎቹ ግብ ጠባቂ አላዛር ማረነ ወደ ውጪ አውጥቶባቸዋል ፤ ከሙከራዉ በኋላ ጦሩ ጫን ብለው በፈጣኝ ሽግግር ወደፊት ሲገሰግሱ ተስተውለዋል።
አጋማሹ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት ሁለቱም ቡድኖች አከታትለው በመልሶ ማጥቃት ሙከራዎችን ሲያደርጉ በ41ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ርቀት ላይ ሆኖ የመታት ኳስ ለጥቂት ከግብ አግዳሚ ከፍ ብላ ያለፈችበት አጋጣሚ ሌላኛው የመቻሎቹ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሆኖ ሲመዘገብ ለሙከራ አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ወደፊት የገሰገሱት ብርቱካናማዎቹ በ43ኛ ደቂቃ ላይ ሄኖክ ሀሰን ከመሃል ሜዳ ብዙም ሳይርቅ ጠንከር ያለ ኳስ ወደግብ መጥቶ ለጥቂት በግቡ ቋሚ በኩል ያለፈባቸው ሙከራ ሲጠቀስ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ የማዕዘን ምት ያገኙት ብርቱካናማዎች ሌላኛውን ሙከራ አድርገዋል ፤ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ አቡበከር ሻሚል በግንባሩ ገጭቶ ለትንሽ ከፍ ብሎበታል።
ጨዋታው በሁለተኛ አጋማሽ ሲመለስ ጦሮቹ ከፍ ያለ ጫናን አሳድረው ለመጫወት የሞከሩበት አጋማሽ ሲሆን በ48ኛው እና በ49ኛው ደቂቃ ላይ አከታትለው ለግብ የቀረበ ሙከራዎችን አድርገዋል።
ምንም እንኳን ጦሩ ብልጫ ቢወስድም ብርቱካናማዎቹ በመከላከሉ ረገድ ተሳክቶላቸው የጦሩን የጥቃት ሲያመክኑ ቆይተው በመልሶ ማጥቃት አልፎ አልፎ ጥቃት ለመሰንዘር ሙከራን አድርገዋል።
በተለይም በ86ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው መስዑድ መሐመድ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታት ኳስ የግብ አግዳሚ የመለሰበት ሙከራ ተጠቃሽ አጋጣሚ ነበር ፤ በዚህም ጨዋታው ያለ አሸናፊ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።