መረጃዎች | 55ኛ የጨዋታ ቀን

በ14ኛው ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ዕለት የሚከናወኑ መርሀ-ግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ሲዳማ ቡና ከ መቐለ 70 እንደርታ

በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሀ-ግብሮች አራት ነጥብ ሰብስበው ደረጃቸው የሚሻሽልላቸው ድል ፍለጋ ወደ ሜዳ የሚገቡት ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ
የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርቧል።

በአስራ ሰባት ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች ብያንስ አንድ ደረጃ የሚያሻሽሉበት ዕድል ለማግኘት ማሸነፍ ይኖርባቸዋል።

ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ በተሰጣቸው ግምት ልክ ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ያልቀረቡት ሲዳማ ቡናዎች ከተከታታይ ሽንፈቶች አገግመው ነጥቦችን መሰብሰብ ጀምረዋል። በአዳማ ከተማ ሊጉ መከናወን ከጀመረ በኋላ የተመቻቸው የሚመስለው ሲዳማ ቡናዎች ከተከታታይ ሦስት ሽንፈቶች በኋላ በሁለት  ጨዋታዎች አራት ነጥቦች በመሰብሰብ መጠነኛ እፎይታ አግኝተዋል።  ሲዳማዎች ከአሰልጣኝ ለውጡ በኋላ በተከታታይ ጨዋታዎች አለመሸነፋቸው ብቻ ሳይሆን ከቀደሙት መርሀ-ግብሮች በአንፃራዊነት የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመራቸው በነገው ጨዋታ ግምት እንዲሰጣቸው ያደርጋል።

ንግድ ባንክ ማሸነፉን ተከትሎ ዳግም ወደ ወራጅ ቀጠና የገቡት መቐለዎች ባሳለፍነው ሳምንት ወልዋሎ ላይ የተቀዳጁት ድል በማስቀጠል ከአደጋው ክልል ለመውጣት ጠንክረው እንደሚጫወቱ ይገመታል።

በአሠልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ የሚመራው መቐለ 70 እንደርታ በ13ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ላይ ወልዋሎን ማሸነፍ ቢችልም እንቅስቃሴው ግን አጥጋቢ አልነበረም። ቡድኑ ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል መመለሱ በጥሩነቱ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም ጨዋታዎች የመቆጣጠር እና ንፁህ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ያለው ውስንነት መቅረፍ ይኖርበታል።

በቅርብ ሳምንታት አደራደሩን ወደ ሦስት የተከላካዮች ጥምረት የለወጠው ቡድኑ ከዚህ ቀደም ደካማ የነበረው የመከላከል አደረጃጀቱ በብዙ መንገድ ማሻሻሉ ባይካድም በአማካይ ክፍሉ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድም ሆነ ዕድሎች ለመፍጠር እየተቸገረ ይገኛል። በአጨዋወቱ ጉልህ የማጥቃት ኃላፊነት መውሰድ የሚገባቸው የመስመር ተመላላሾች አጠቃቀም ማስተካከልም በነገው ዕለት የሚጠበቅባቸው ስራ ነው። እንዲሁም አሠልጣኙ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ እንዳሉትም ቡድኑ ላይ ሲታይ የነበረው መቻኮል ወይም ትዕግስት አልባ እንቅስቃሴ ገደብ ማበጀትም በነገው ዕለት የሚጠብቃቸው ሌላው ስራ ነው።

በሲዳማ ቡና በኩል ከብርሃኑ በቀለ ቅጣት ውጪ ሁሉም ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።በመቐለ 70 እንደርታዎች በኩል አምበሉ ያሬድ ከበደ ከሦስት ጨዋታዎች ቅጣት ሲመለስ ያብስራ ተስፋዬ፣ መናፍ ዐወል፣ አሸናፊ ሀፍቱ፣ ክብሮም አፅብሀ እና አማኑኤል ልዑል ግን በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም። የኪሩቤል ኃይሉ እና ያሬድ ብርሀኑ መሰለፍም  አጠራጣሪ ነው።

ቡድኖቹ እስካሁን ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት ሁለት ጊዜ ድል አርገዋል። በግንኙነታቸው ከተቆጠሩት 11 ጎሎች መቐለ ስድስቱ ሲያስቆጥር ሲዳማ አምስቱን አስቆጥሯል።

ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ ወላይታ ድቻ

በአንድ ነጥብ በሊጉ ግርጌ የሚገኘው እና የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድሉን በመጠባበቅ ላይ የሚገኘው ወልዋሎ እና ከተከታታይ ሳምንታት የሽንፈት አልባ ጉዞ በኋላ ሽንፈት ያስተናገደው ወላይታ ድቻ የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሀ-ግብር ነው።

ወልዋሎዎች ከአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም መምጣት በኋላ ውስን መሻሻል ማሳየት ቢችሉም
ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ካሳካኩት አንድ ነጥብ ውጭ ማስመዝገብ አልቻሉም። በደርቢው ጨዋታ ከሌሎች ጨዋታዎች በአንፃራዊነት የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳየው ቡድኑ በጨዋታው ጥቂት የማይባሉ ዕድሎች መፍጠር ቢችልም ከጉጉት የመነጨ የሚመስለው በግብ ፊት ያለው ደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ትልቁ ደካማ ጎኑ ነበር። ኳስ እና መረብን ካገናኘ አምስት ጨዋታዎች ያለፉት ወልዋሎ በነገው ጨዋታም ከጠንካራ የተከላካይ ክፍል ካለው ቡድን ጋር እንደመገናኘቱ ይህንን ችግሩን በምን መልኩ ቀርፎ ይመጣል የሚለው ጉዳይ የሚያሳስበው ይሆናል።

ቡድኑ ለከርሞ በሊጉ የመትረፍ ዕድሉ ከአሁኑ ለማለምለም እና ካለበት የውጤት ማጣት በቶሎ ለመላቀቅ ከወዲሁ ነጥቦችን መሰብሰብ በሚገባው ሰዓት ላይ እንደመገኘቱ በብዙ ረገድ ተሻሽሎ መቅረብ ግድ ይለዋል።

በመጨረሻው ሳምንት ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ሽንፈት ያስተናገዱት ወላይታ ድቻዎች ከአራት ሳምንታት በኋላ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ቢጫዎቹን ይገጥማሉ።

በሊጉ ከኳስ ውጭ ብዙ የሜዳ ክፍል ከሚያካልሉ እና በታታሪ ተጫዋችቾ ከተገነቡ ክለቦች አንዱ የሆነው ቡድኑ ለጥንቃቄ ከፍ ያለ ትኩረት የሰጠ እና በመስመር ተሰላፊዎቹ ፍጥነት ላይ የተመሰረተው የመልሶ ማጥቃት ዋነኛው የግብ መፍጠሪያ መንገዱ መሆኑ ነገም የሚቀጥል ይመስላል። ወላይታ ድቻዎች በንፅፅር ደካማ የመከላከል ክፍል ካለው እና በውድድር ዓመቱ 17 ግቦች ካስተናገደ ቡድን እንደመግጠማቸው ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ ባይገመትም በመጨረሻው መርሀ-ግብር ከነበራቸው የሦስተኛው ሜዳ ክፍል እንቅስቃሴ በብዙ ረገድ አሻሽለው መቅረብ ይኖርባቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ተጋጣሚያቸው ወልዋሎ በአንዳንድ ጨዋታዎች ሳይጠበቅ ወደ ራሱ የግብ ክልል የተጠጋ አቀራረብ የነበረው ቡድን እንደመሆኑ ከመልሶ ማጥቃት በዘለለ ከወዲሁ ሌሎች የግብ መፍጠርያ መንገዶች ማበጀት ይኖርበታል።

በወልዋሎ በኩል ዳዋ ሆቴሳ፣ ሱልጣን በርሐ እና ታዬ ጋሻው በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም ፤ በወላይታ ድቻ በኩል አብነት ደምሴ ከቅጣት ይመለሳል፤ ባለፈው ጨዋታ ላይ ከግቡ ቋሚ ጋር ተጋጭቶ ጉዳት ያስተናገደው አብነት ይስሐቅ ግን ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን ዋና ግብ ጠባቂው ቢንያም ገነቱ በተመሳሳይ ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ልምምድ ቢመለስም ለነገው ጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ በመሆኑ በሦስተኛ በረኛቸው አብነት ሀብታሙ እየተመሩ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል። መልካሙ ቦጋለም ለነገው ጨዋታ እንደማይደርስ ሲጠበቅ የተቀሩት የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸውን ያገኘነው መረጃ ያመላክትል።

የተሰረዘውን የ2012 ውድድር ዘመን ሳይጨምር ሁለቱ ቡድኖች 4 ጊዜ ተገናኝተው ሁሉንም አቻ ተለያይተዋል ፤ እኩል ሦስት ሦስት ጎሎችም አስቆጥረዋል።