ሪፖርት | ሲዳማ ቡና እና መቐለ 70 እንደርታ ነጥብ ተጋርተዋል

የሊጉ አስራ አራተኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀን መርሐ ግብር ሲዳማ ቡናን ከመቐለ 70 እንደርታ አገናኝቶ ያለ ጎል ተጠናቋል።

በሲዳማ ቡና በኩል ከባንክ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ በሬድዋን ናስር እና ሳሙኤል ሳሊሶ ምትክ አበባየሁ አጅሶ እና አስቻለው ሙሴ ጨዋታውን ሲጀምሩ በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ወልዋሎን ከረታው አሰላለፍ የሁለት ተጫዋች ለውጥ በማድረግ በክብሮም አፅብሀ እና ተመስገን በጅሮንድ ምትክ ያሬድ ከበደ እና ኬኔዲ ገብረፃዲቅ በመጀመርያ አሰላለፍ ተካተዋል።

የመጀመርያው አጋማሽ የተቀዛቀዘ የጨዋታ እንቅስቃሴ የታየበት ቢሆንም ሲዳማ ቡና በአንፃራዊነት ብልጫ ያሳየበት እና ጥቂት ሙከራዎችን ያደረገበት ነበር።

በ14ኛው ሀብታሙ ታደሰ ያመቻቸለትን ኳስ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ መትቶ የቀኝ ቋሚ ገጭቶ ሲመለስ ሀብታሙ አግኝቶት ቢመታም ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ ሲዳማዎችን በጊዜ መሪ ሊያደርግ የሚችል ሙከራ ነበር።

ከዚህ ሙከራ በኋላ ሲዳማዎች በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ቀጥለው ተጨማሪ ሙከራዎች ማድረግ የቻሉ ቢሆንም ኳስ እና መረብ ማገናኘት አልቻሉም። በ22ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ አበባየሁ አጅሶ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ የወጣበት እንዲሁም በ36ኛው ደቂቃ ኢማኑኤል ላርዬ ከርቀት ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራዎች ተጠቃሽ ናቸው ።

በሁለተኛው አጋማሽ መቐለ 70 እንደርታዎች በመጀመርያ አጋማሽ የነበረባቸውን የማጥቃት ድክመት በመጠኑ አሻሽለው በመግባት የጎል እድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። በተለይም የመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች በመልሶ ሜጥቃት የሲዳማ ቡና የጎል ክልል ቶሎ ቶሎ ቢደርሱም በበቂ ሁኔታ አደጋ መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ከመጀመርያው አጋማሽ በአንፃራዊነት ተቀዛቅዘው የመጡት ሲዳማ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥር ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ ነበሩ። ሆኖም በ67ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻማውና ሀብታሙ ታደሰ ሞክሮ የጎሉ አግዳሚ ከመለሰበት ሙከራ ውጪ በበቂ ሁኔታ የመቐለን የኋላ ክፍል መፈተሽ ሳይችሉ ቀርተዋል። ጨዋታውም ጎል ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።