ሪፖርት | የጦና ንቦቹ ከአምስት ሳምንት በኋላ ከድል ጋር ታርቀዋል

ወላይታ ድቻዎች ከናፈቃቸው ድል ጋር የታረቁበትን ውጤት በወልዋሎን በማሸነፍ ሲያሳኩ ወልዋሎዎች በአንፃሩ የዓመቱ የመጀመርያ ድላቸውን ለማሳካት ሌላ ጨዋታ ለመጠበቅ ተገደዋል።

በመቐለ 70 እንደርታ ሽንፈት ማግስት ወልዋሎ ዓ/ዩ ከስብስባቸው የአንድ ተጫዋች ለውጥ በማድረግ ሱልጣን በርሄን በጋዲሳ መብራቴ ቀይረው ወደ ሜዳ ሲገቡ በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች በኢትዮጵያ መድን ከደረሰባቸው ሽንፈት ከተጫወተው ስብስባቸው
የሦስት ተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ግብጠባቂ አብነት ይስሐቅ፣ ምንተስኖት አስፋው እና መሳይ ሰለሞን በማሳረፍ በምትኩ በግብጠባቂ አብነት ሀብቴ፣ ኬኔዲ ከበደ እና ጸጋዬ ብርሀኑ በመያዝ ለፍልሚያው እራሳቸውን አዘጋጅተዋል።

ፌደራል ዋና ዳኛ መለሰ ንጉሴ በመሩት የምሽቱ ጨዋታ አጀማመራቸውን ከእንቅስቃሴ ጋር ያሳመሩት ወላይታ ድቻዎች በ8ኛው ደቂቃ የመጀመርያ ጎላቸውን አግኝተዋል። ኬኔዲ ከበደ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ከቀኙ ጠርዝ የላከውን ኳስ የወልዋሎ ተከላካይ ቃሲም ረዛቅ በግርንባሩ ማራቅ ሲገባው ሳያርቀው ቀርቶ የሰራውን ስህተት ተከትሎ ያሬድ ደርዛ በተረጋጋ ሁኔታ ኳሱን ወደ ሳጥን ገፍቶ ኳስና መረብን አገናኝቷል።

በእንቅስቃሴ ረገድ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ኳሱን አደራጅተው በመውጣቱ ረገድ ያልተቸገሩት ወልዋሎዎች የመጨሻው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ኳሳቸው እየተቋረጠ አደጋ ለመፍጠር ሲቸገሩ እንመልከት እንጂ እንቅስቃሴያቸው ጥሩ የሚባል ነበር። ሆኖም በ18ኛው ደቂቃ ቢጫ ለባሾቹ ከራሳቸው ሜዳ ለመውጣት በሚያደርጉት ቅብብሎች መውጫ ቀዳዳ ያሳጧቸው ወላይታ ድቻዎች ካርሎስ ዳምጠው በግንባሩ ሸርፎ ለብዙአየሁ ሰይፉ ሳጥን ውስጥብቻውን ከግብጠባቂው ጋር ተገናኝቶ በረከት እንደምንም ያወጣበት ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል መሆን የሚችል ነበር።

የጨዋታው ሂደት ከመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች ብዙም የተለየ እንቅስቃሴ ባይኖረውም የጦና ንቦቹ ከራሳቸው ሜዳ በረጅሙ ለአጥቂዎቻቸው በተለይ ካርሎስ ዳምጠውን መሰረት ያደረጉ ኳሶች አደጋ ይፈጥሩ ነበር። በ37ኛው ደቂቃ ከወላይታ ድቻው ግብጠባቂ አብነት ሀብቴ በቀጥታ የተላከውን ካርሎስ ዘሎ በግንባሩ የጨረፈውን ያሬድ ደርዛ በሜዳው የግራው ጠርዝ ሳጥን ውስጥ በመግባት ወደ ውስጥ የጣለውን ከጎሉ በቅረብ ርቀት የነበሩት ካርሎስ ዳምጠው እና ቴዎድሮስ ታፈሰ ሲገባበዙ ቴዎድሮስ ታፈሰ ሳይጠቀምበት ለጥቂት በግቡ ቋሚ ታኮ የወጣው ለጦና ንቦቹ ሁለተኛ ጎል መሆን የሚችል ነበር።

በሁለቱ የሜዳ ክፍል እንቅስቃሴያቸው መልካም የነበረ ቢሆን ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ በሚባክኑ ኳሶቻቸው ምክንያት ወልዋሎዎች በመጀመርያው አጋማሽ የጠራ የግብዕድል ሳይፈጥሩ 1-0 እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከመጀመርያው አጋማሽ እጅግ በወረደ መልኩ ህይወት አልባ የሆነ የጨዋታ እንቅስቃሴ ያስመለከቱን ሁለቱ ቡደኖች በጎል ሙከራ እረገድ አይነ አፋር ሆነው የጨዋታው ስልሳ አምስተኛው ደቂቃ መዝለቅ ችሎ ነበር። በተወሰነ መልኩ በሁለቱም ቡድኖች የተጫዋቾች ቅያሪ ካደረጉ በኋላ ጨዋታው ጋል ወደ አለ ፉክክር ያመራ ሲሆን ወልዋሎዎች በ66ኛው ደቂቃ ወጣቱ አጥቂ ናትናኤል ሰለሞን ጠንከር ባላለ ምቱ ወደ ጎል የመታውን ኳስ ግብጠባቂው አብነት በቀላሉ የያዘበት ለወልዋሎች ተጠቃሽ ለጎል የቀረበ ሙከራ ነበር።

ወላይታ ድቻዎች ከጨዋታው እፎይታ ያገኙበትን ጎል በ84ኛው ደቂቃ አግኝተው መሪነታቸውን ወደ ሁለት ጎል ከፍ አድርገዋል። ከማዕዘን ምት ቴዎድሮስ ታፈሰ በጥሩ መንገድ መሬት ለመሬት ሰው ፈልጎ የላከውን ፍፁም ቅጣት ምት መምቻው ላይ ኳሱን ያገኘው ተቀይሮ የገባው የመስመር አጥቂው ብስራት በቀለ ቦታ አይቶ በጥሩ አጨራስ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።

ከዚህ ጎል መቆጠር በኋላ ብዙም የተለየ ነገር ባይኖርም 89ኛው ደቂቃ ላይ ወልዋሎ ዓ/ዩ ዋና አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ባሳዮት ያልተገባ ባህሪ በቀጥታ ቀይ ጋር ከሜዳ እንዲወገዱ ተደርጎ ጨዋታውም ወላይታ ድቻ 2-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።