ሪፖርት | ቡናማዎቹ ወደ ድል ተመልሰዋል

ናይጄሪያዊው አማካይ ዲቫይን ዋቹኩዋ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ቡናማዎቹ ወደ ድል ሲመለሱ ዐፄዎቹ ከአምስት ጨዋታ በኋላ ሽንፈት አስተናግደዋል።

ፋሲል ከነማ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ በኋላ ባለፈው ሳምንት አራፊ ሆኖ ዛሬ ሲመለስ ከባለፈው ስብስቡ የአምስት ተጫዋች ቅያሪዎች አድርጓል። ግብጠባቂ አማስ  ኦባሶጊ፣ ኪሩቤል ዳኜ፣ ዮናታን ፍስሃ፣ አሚር ሙደሲር፣ በረከት ግዛው እና ቃልኪዳን ዘላለምን በማሳረፍ በምትኩ  ግብጠባቂ ዮሐንስ ደርሶ ፣ ሀቢብ  መሀመድ ፣ አቤል እንዳለ ፣ ብሩክ አማኑኤል ፣ ዳግም አወቀ እና ጃቪር ሙሉን በመያዝ ወደ ሜዳ ሲገቡ በአንፃሩ በኢትዮጵያ ከድሬደዋ ከተማ ጋር በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀው ስብስባቸው ምንም አይነት የተጫዋች ለውጥ ባለማድረግ ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።


ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በመሩት በዚህ ጨዋታ በሁለቱም በኩል የኳስ ቁጥጥሩን ብልጫ በመውሰድ በሚገኙ ቀዳዳዎችን በመፈለግ የግብ አጋጣሚዎች ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ጨዋታውን ሳቢ መልክ እንዲኖረው ያስቻለው ሲሆን 5ኛው ደቂቃ ፋሲል ከነማ ያገኘውን ማዕዘን ምት ተከትሎ ተመስገን ካስትሮ እና ኦካይ ጁል ኳሱን ለማግኝት በሚያደርጉት ዝላይ እርስ በእርስ ተጋጭተው በተፈጠረ ጉዳት ጨዋታው ለአምስት ደቂቃዎች ያህል ለመቋረጥ ተገዶ ነበር።

ተጫዋቾቹ ህክምና አግኝተው ጨዋታው ከቀጠለ በኋላ በ17ኛው ደቂቃ የዐፄዎቹ የመስመር አጥቂ ማርቲን ኪዛ ከቀኝ መስመር የሜዳው ክፍል ፍጥነቱን ተጠቅሞ ሳጥን ውስጥ በመግባት ከእርሱ በተሻለ ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ጌታነህ ከበደ ለመስጠት ከማሰብ ይልቅ በቀጥት ራሱ መቶት ወደ ውጭ የወጣው በጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ሊሆን ችሏል።

በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ፋሲል የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ የሚደርሱት ቡናማዎቹ በ21ኛው ደቂቃ በግራ መስመር ተከላካዩ በፍቃዱ ዓለማየሁ አማካኝነት ለጎል የቀረበ ሙከራ አድርገዋል ፤ የጨዋታው እንቅስቃሴ አሰልቺ የሚባል ባይሆንም ግብጠባቂዎችን የሚፈትኑ የጠሩ የጎል ሙከራዎችን በማድረግ በኩል ሁለቱም ደካሞች የነበሩ ቢሆንም ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንፃራዊነት በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ተደጋጋሚ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በመድረስ ረገድ የተሻሉ ሆነው የመጀመርያው አጋማሽ ያለ ጎል ለዕረፍት ተጠናቋል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቃልኪዳን ዘላለምን ቀይረው በማስገባት የማጥቃት አቅማቸውን ለማሳደግ ቢያስቡም ከመጀመርያው አጋማሽ ብዙም የተለየ ነገር ሳያሳዩን በተመሳሳይ አጨዋወት ሲዘልቅ። ኢትዮጵያ ቡናዎች 55ኛው ደቂቃ ከሜዳው ቀኝ ከሳጥን ውጭ በግምት ከ19 ሜትር  ያገኙትን ቅጣት ዲቫይን ዋቹኩዋ በግሩም ሁኔታ ቢመታውም የግቡ አግዳሚ ጎል እንዳይሆን አግዶታል።

ብልጫ ወስደው ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ብናማዎቹ የሚገባቸውን ጎል 66ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። አንተነህ ተፈራ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ በሜዳው የግራ ክፍል ሳጥን ውስጥ በመግባት የመታውን ኳስ ግብጣቂው ዮሐንስ እንደምንም የመለሰውን ዲቫይን ዋቹኩዋ አግኝቶ በጥሩ አጨራረስ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።


ፋሲል ከነማዎች ጎሉ ከተቆጠረባቸው በኋላ በአንፃራዊነት ወደ ፊት ለመሄድ ቢያስቡም ኳሶቻቸው እየተቆራረጡ የረባ የጎል ዕድል መፍጠር ረገድ ሲቸገሩ አይተናል። በቡናማዎቹ በኩል በ80ኛው ደቂቃ አንተነህ ተፈራ በሁለት አጋጣሚ ያገኘውን ጥሩ የግብ ዕድል ግብጠባቂው ዮሐንስ ያመከነበት የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነው። የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች ከቆሙ ኳሶች በፋሲል በኩል የሚሰነዘርባቸውን ጥቃቶች በመቆጣጠር የሚፈልጉት ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል።