ሪፖርት | ምዓም አናብስት ወሳኝ ድል ተጎናጽፈዋል

ምዓም አናብስቶች በቤንጃሚን ኮቴ መጀመሪያ አጋማሽ ግብ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በመርታት ወደ ድል ተመልስዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ14ኛው ሳምንት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከተረቱበት ጨዋታ ላይ ከተጠቀሙበት ቋሚያቸው አንድ ለውጥ ብቻ አድርገው አበባየሁ ዩሐንስን በሀብታሙ ሸዋለም ተክተው ሲገቡ መቐለ 70 እንደርታ ከሲዳማ ቡና ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ቋሚ ስብስባቸው ሶስት ለውጥ በማድረግ ለውጥ በማድረግ ሰለሞን ሀብቴን በሄኖክ አዱኛ ኬኔዲ ገብረፃዲቅን በኪሩቤል ሀይሉ ሄኖክ አንጃውን በያሬድ ብርሀኑ ተክተው ገብተዋል።

ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ከግብ ማግባት እንቅስቃሴዎች ጋር እያስመለከተ በጀመረው በመጀመራያው በአጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በመጀመራያውቹ ደቂቃዎች በጥንቃቄ ሲጫወቱ ቢያስመለከትም የኋላ ኋላ ወደ ጨዋታው በመመለስ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ሲደርሱ አስመልክቷል። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ የተሻለ እንቅሰቃሴ የነበራቸው ሲሆን 15ኛው ደቂቃ ላይ የቆመ ኳስ ተሻምቶ የምዓም አናብስቶቹ ግብ ጠባቂ ሲመልስባቸው ምዓም አናብስቶችም በ24ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ከሳጥን ውጪ ሆኖ ያደረገው ሙከራ ለትንሽ ከፍ ብሎበታል።

ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅሰቃሴ እያስመለከተ ጨዋታው ሲቀጥል የግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችን በመፍጠር ረግድ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአንፃራዊነት የተሻለ ነበር። ምዓም አናብስቶችም በረጃጅም ኳሶች በፍጥነት ወደ እየደረሱ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ አስተውለናል። የጥረታቸው ውጤት የሆንችዋን ግብም መረብ ላይ አሳርፈዋል። ጨዋታው 37ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ቤንጃሚን ኮቴ በግንባሩ ገጭቶ ወደግብነት ቀይሮ መሪ አድርጓቸዋል።

ከእረፍት መልስ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተሻለ ጥንካሬ ቀርበው ሙከራዎችን አድርገዋል። በ47ኛው ደቂቃ ላይ ፍቃዱ አለሙ ተከላካዮችን ቀንሶ በማለፍ ሳጥን ውስጥ ሆኖ አክርሮ የመታውን ኳስ ሶፎንያስ ሰይፈ ሲመልስበት እንዲሁም በ53 ደቃቃ ላይ በድጋሚ ፍቃዱ አለሙ ከአቤል ሀብታሙ የተሻገረለትን ኳስ በደረቱ አቁሙ በግሩም ሁኔታ ዞሮ የመታው ሙከራ እላማውን ሳይጠበቅ የቀረበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ነበር። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በጥሩ ኳስ ቅብብል ፈጣኝ ሽግግር እያደረጉ የምዕም አናብስቶችን ግብ ሳጥን በተደጋጋሚ ረግጠው ለተከላካይ ፈታኝ የሆኑ ሙከራዎችን በማድረግ ሲጠመዱ በ64ኛው ደቂቃ ላይ ከመሃል ሜዳ አከባቢ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ አቤል ሀብታሙ አግኝቶ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠበቅ ደካማ ሙከራ አድርጎ ሶፎንያስ ሰይፈ በቀላሉ የተቆጣጠረበት አጋጣሚ ይታወሳል።

በ73ኛው ደቂቃ ላይ የቆመ ኳስ ተሻምቶ የመቐለ 70 እንደርታ ተከላካዮች ለማራቅ ጥረት ሲያደርጉ ፍቃዱ አለሙ ኳሷን አየር ላይ እንዳለች ጠንከር ያለ ኳስ ወደግብ መጥቶ ተከላካዮቹ እንዴትም ተረባርበው ሲያርቁባቸው በ78 ደቂቃ ላይ በድጋሚ ከመሃል አከባቢ የተሻገረውን ኳስ ይዘው ገብተው ያደረገውን ሙከራ ሶፎንያስ ሰይፈ በብልሃት መልሶባቸዋል። እንዲሁም በ80ኛው ደቂቃ ሄኖክ ገብረህይወት ከቀኝ መስመር አከባቢ ያሻማውን ኳስ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በግንባሩ ገጭቶ ሙከራ ሲያደርግ ለጥቂት በግራ ግብ ቋሚ ብረት አጠገብ አልፋበታለች።

ምዓም አናብስቶች በሁለተኛው አጋማሽ ወደኋላ አፈግፍገው ወደ መከላከሉ አድልተው የተጫወቱ ሲሆን አልፈው አልፈው በመልሶ ማጥቃት ወደፊት ለመሄድ የሞከሩ ቢሆንም ይሄ ነው የሚባል ሙከራ በፍፁም አላስመለከቱም። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአጋማሹ በአንፃራዊነት በኳስ ቁጠጥርም ሆነ የግብ ማግባት ሙከራ በማድረግ ፍፁም  በላይነት ወስደው በሙከራውችም ደምቀው ቢያመሹም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠረባቸው ግብ ሽንፈት ሊያስተናግዱ ችለዋል። በዚህም ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ ቤንጃሚን ኮቴ ባስቆጠራት ግብ ለምዓም አናብስቶች ወሳኝ ሶስት ነጥብ በማጎናፀፍ ተጠናቋል።