ሀዲያ ሆሳዕና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በእዮብ ዓለማየሁ ብቸኛ ግብ በመርታት በጊዜያዊነት የሊጉን መሪነት መረከብ ችለዋል።
ሀዲያ ሆሳዕና በ13ኛው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ ተጋርተው ወደ ዕረፍት ካመራው ቋሚ ስብስባቸው ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ደስታ ዋሚሾን በእዮብ ዓለማየሁ ተክተው ሲቀርቡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ14ኛው ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከረቱበት ቋሚያቸው አምስት ለውጦችን በማድረግ ተስፋዬ ታምራትን በእንዳለ ዩሐንስ ፣ ካሌብ አማንክዋን በተመስገን ተስፋዬ፣ ብሩክ እንዳለን በቢኒያም ካሣሁን ፣ ዮናስ ለገሰን በኪቲካ ጅማ እና ቢኒያም ጌታቸውን በሃይከል ደዋሙ ተክተው ቀርበዋል።
ወደፊት በሚደረጉ ፈጣን እንቅስቃሴዎች በጀመረው ጨዋታው ንግድ ባንኮች በ12ኛው ደቂቃ በግራ መስመር በኩል የተሻማውን ኳስ ሳጥን ውስጥ አዲስ ግደይ በግንባር ገጭቶ የሞከረው እንዲሁም በ16ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ሳይመን ፒተር ያደረጋት ሙከራ ተጠቃሽ ነበሩ።
ነብሮቹ በአንፃሩ በ15ኛው ደቂቃ ላይ ሰመረ ሀፍተይ ተጨራርፋ የደረሰችውን ኳስ ይዞ ወደ ሳጥን ውስጥ በመግባት ያደረገውን ሙከራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ግብ ጠባቂ ያዳነበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ነበረች።
አንፃራዊ የበላይነት የነበራቸው ነብሮቹ በ21ኛው ደቂቃ ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። ብሩክ በየነ የንግድ ባንክ የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች በቀላሉ አታሎ በማለፍ ያሻገረለትን ኳስ እዮብ ዓለማየሁ በድጋሚ ተከላካዮችን አይቶ በመቀነስ በግሩም አጨራረስ ወደግብነት ቀይሮታል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ በሁለቱ ቡድኖች በኩል የተሻለ አውንታዊ እንቅስቃሴ ቢታይም ተጨማሪ የግብ ዕድሎችን ሳንመለከት አጋማሹ ተገባዷል።
ጨዋታው ከእረፍት ሲመለስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ጫና ሲያሳድሩ 50ኛው ደቂቃ ላይ ከመሃል ሜዳ አካባቢ የተሻገረውን ኳስ ኪቲካ ጅማ ደርሶ በደካማ እግሩ ሞክሮ ዒላማዋን ሳትጠብቅ የቀረችዋ ኳስ ስትጠቀስ ምንም እንኳን ንግድ ባንክ በቅብብሎች ወደፊት በመሄድ ብልጫ ቢኖራቸውም ጨዋታው ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ሳያስመለክት እስከ ሰባኛው ደቂቃ ድረስ ዘልቋል።
ነብሮቹ የሚያገኙትን እድል ወደ ግብ ለመቀየር በረጃጅም ኳሶች በመልሶ ማጥቃት ወደፊት ይሂዱ እንጂ ሙሉ ትኩረታቸው መከላከሉ ላይ አድርገው ሲንቀሳቀሱ አስተውለናል።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታው እንቅስቃሴ አሰልቺ የሚባል ባይሆንም ፈታኝ የሆኑ የጠሩ የግብ ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ሁለቱም ቡድኖች ደካማ የነበሩ ቢሆንም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንፃራዊነት በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል በመድረስ የተሻሉ ሆነው ጨዋታው በነብሮቹ የበላይነት ተቋጭቷል።