ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን አራተኛ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል

ኢትዮጵያ መድን ባህርዳር ከተማን በረመዳን የሱፍ ብቸኛ ግብ በማሸነፍ አራተኛ ተከታታይ ድላቸውን አሳክተዋል።

ባህርዳር ከተማ በ13ኛው ሳምንት ሀዋሳ ከተማን በመርታት ወደ ዕረፍት ካመሩበት ቋሚ አሰላለፋቸው ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ሲቀርቡ በተመሳሳይም ኢትዮጵያ መድንም እንዲሁ በ14ኛው ሳምንት ሀዋሳ ካሸነፉበት ቋሚ አሰላለፋቸው ለውጥ ሳያደርጉ ቀርበዋል።


በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ኢትዮጵያ መድን በፈጣን ሽግግሮች ጫና በመፍጠር በጀመረው ጨዋታ ገና በማለዳው ነበር ሙከራዎችን መሰንዘር የጀመሩት ፤ በ6ኛው ደቂቃ ላይ ሚሊዮን ሰለሞን ከርቀት የሞከራት ጠንካራ ኳስ እንዲሁም 12ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ ያሻማውን ኳስ አቡበከር ሳኒ መረጋገት ተስኖት በግንባሩ ለማቆም ሲሞክር ግብ ጠባቂው የያዘበት አስቆጪ ዕድል ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያ መድን በአጋማሹ በኳስ ቁጥጥር ሆነ በሙከራ ረገድ ተሽለው የታዩ ሲሆን በተለይም በ31ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ካሳይ በግራ መስመር በኩል ያሻማውን ኳስ አቡበከር ሳኒ ወደ ግብ ፔፔ ሰይዶ ያወጣበት ሌላኛው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።

ባህርዳር ከተማዎች በአንፃሩ በአጋማሹ ደካማ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን በብዙ መልኩ በአጋማሹ በተጋጣሚያቸው ጥላ ስር ያሳለፉበት ነበር።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስም ሁለቱም ቡድኖች በአንፃራዊነት ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተመልክተናል።

በዚህም በመጀመሪያው አጋማሽ ደከም ያለ እንቅስቃሴ ሲያስመለክቱ የነበሩት የጣናው ሞገዶች በተሻለ አቀራረበ ይዘው በመቅረብ ወደፊት ሲሄዱና በአጋማሹ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው ተደጋጋሚ ጥቃቶችን የሰነዘሩበት ነበር።

በብዙ መመዘኛዎቹ የኋላ ኋላ እየተቀዛቀዘ በመጣው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኖች በበኩላቸው እንደመጀመሪያው አጋማሽ ኳስ ተቆጣጥረው እንደልብ መጫወት አቅቷቸው ቢታይም በመጨረሻም አሸናፊ የሆኑበት ግብ አግኝተዋል።

79ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል የተገኘውን ኳስ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ የነበረው ረመዳን የሱፍ በጠንካራ ምት ወደ ግብነት ቀይሮ መሪ ቡድኑ መሪ እንዲሆን አስችሏቸዋል።

በረመዳን የሱፍ ግብ የተነቃቁ የመሰሉት ኢትዮጵያ መድኖች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ደጋግመው የባህርዳርን የግብ ክልል ቢጎበኙም ተጨማሪ ግብ ማግኘት ሳይችሉ ጨዋታው 1-0  ተጠናቋል።