በመውረድ ስጋት ውስጥ ሆነው የተገናኙት ሀዋሳ ከተማ እና ወልዋሎ ዓ/ዩ ያደረጉት ጨዋታ በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ሀዋሳ ከተማ በኢትዮጵያ መድን ከተሸነፈበት ስብስቡ የሁለት ተጫዋቾችን ቅያሪ አድርጓል ግብጠባቂ ምንተስኖት ጊንቦ እና ሰለሞን ወዴሳ በማሳረፍ ግብጠባቂ ሰዒድ ሀብታሙ እና ወንድማገኝ ማዕረግ በመተካት ከናፈቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ ወደ ሜዳ ሲገቡ ወልዋሎ ዓ/ዩ በተመሳሳይ በወላይታ ድቻ ከደረሰባቸው ሽንፈት ማግስት ሁለት ተጫዋቾችን ቀይረዋል ዳዊት ገብሩ እና ናትናኤል ሰለሞን በናሆም ኃይለማርያም እና በዳዋ ሆጤሳ ተክተው የሊጉን የመጀመርያ ሦስት ነጥብ ለማሳካት ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ፌደራል ዋና ዳኛ ሙሉቀን ያረጋል በመራው በዚህ ጨዋታ ዕድሎችን በአግባቡ አይፍጠሩ እንጂ በፍላጎት ደረጃ እና ደጋግመው ወደ ፊት በመድረስ በኩል ወልዋሎ ዓ/ዩ የተሻሉ መሆናቸውን የመጀመርያው ሃያ ደቂቃዎች ማሳየት ችለዋል። በአንፃሩ በሀዋሳዎች በኩል ከራሳቸው ሜዳ ኳሱን ይዘው ለመውጣት ከሚያደርጉት ቅብብሎሽ ባሻገር በተቃራኒው ቡድን ሜዳ በመግባት አደጋ ለመፍጠር የነበራቸው ጥራት ከሌላው ጊዜ የተቀዛቀዘ ነበር።
በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የነበራቸውን እንቅስቃሴ ያስቀጠሉት ቢጫ ለባሾቹ የመጀመርያ ጎላቸውን በ24ኛው ደቂቃ በማግኘት መነቃቃት ችለዋል። ከሜዳ ከግራ መስመር የተገኘውን ቅጣት ምት ጋዲሳ መብራቴ ያሻማውን ዳዋ በእጁ ያቀዘቀዛት በሚመስል አካኋን ኳሱን ያገኘው ተከላካይ ቃሲም ረዛቅ በጥሩ እይታ ወደ ውስጥ ያቀበለውን ናትናኤል ዘለቀ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።
ከጎሉ በኋላ የጥንቃቄ አጨዋወት የመረጡት ወልዋሎዎች በራሳቸው ሜዳ በቁጥር በዝተው ሲከላከሉ በአንፃሩ ሀይቆቹ ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በሙከራ መታጀብ የጀመረ ሲሆን 36ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር የተሻገረውን ሳጥን ውሰጥ ዓሊ ሱሌማን በቀኝ እግሩ በቀጥታ የመታወን የግቡ አግዳሚ የመለሰበትን በድጋሚ ኳሱን ያገኘው ዓሊ ሳይጠቀምበት የቀረው የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። እንዲሁም 45ኛው ደቂቃ በሁለት አጋጣሚ ቢንያም በላይ ከቀኝ መስመር የሰነጠቀለትን ኳስ አማኑኤል ጎበና ወደ ጎል ሲመታው ተከላካዮች ተደርበው ሲያወጡት የተሰጠውን ማዕዘን ምት ቢንያም ያሻገረውን ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ወንድማገኝ ማዕረግ በግንባሩ በመግጨት ጎል አስቆጠረ ሲባል ግብጠባቂው በረከት አማረ በቀላሉ የያዘበት ተጠቃሽ ነበር።
ሀዋሳዎች ብልጫ ወስደው ጎል ፍለጋ ጥረት እያደረጉ ባለበት ሁኔታ ተከላካያቸው በረከት ሳሙኤል ዳዋ ሆጤሳ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱ ቡድኑን ዋጋ ሊስከፍለው እንደሚችል ተገምቶ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ከዕረፍት ጨዋታው እንደተመለሱ አሰልጣኝ ወንድማገኝ የሦስት ተጫዋቾች እንዲሁም የታክቲክ ለውጥ አድረወገዋል። ፍቃደስላሴ ደሳለኝ፣ አማኑኤል ጎበናን እና ቢንያም በላይን በፀጋአብ ዮሐንስ ፣ አቤኔዘር እና እስራኤል እሸቱ ያደረጉት ቅያሪ ተሳክቶላቸው በፍጥነት ነበር ጎል ያስቆጠሩት። 47ኛው ደቂቃ ተባረክ ቀኝ መስመር ያቀበለውን ተቀይሮ የገባው እስራኤል ተከላካዮችን በፍጥነት ቀድሞ ቡድኑን አቻ ማድረግ የቻለበትን ጎል አስገኝቷል። እስራኤል ጎሉን ከማስቆጠሩ በፊት ከነጉዳቱ አጋጥሞት ነበርና ለተሻለ ህክምና በአንቡላን አምርቷል።
የጨዋታው መልክ በጉዳትም በተለያዮ ምክንያቶች እየተቆራረጠ መቀዛቀዝ ቢያሳይም 68ኛው ደቂቃ የወልዋሎ አጥቂዎች ሳጥን ውስጥ ክፍት ቦታ ሲፈልጉ ዳዋ ያቀበለውን ጋዲሳ መብራቴ ካስጥኑ ውጭ በጥሩ ሁኔታ የመታውን የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ለቢጫ ለባሾቹ የሚያስቆጭ ነበር።
የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ወልዋሎዎች የቁጥር ብልጫቸውን ተጠቅመው አንዳች ነገር ያሳያሉ ቢባልም ብዙም የተለየ ነገር ሳያስመለክቱን ሲቀር በአንፃሩ ሀዋሳዎች በቁጥር እንደማነሳቸው የአቻው ውጤት ለእነርሱ አስፈላጊ መሆኑን በሚያሳይ መልኩ ታክቲካሊ ጨዋታውን የማባከን እንቅስቃሴ ቢያሳዮም በጭማሪው ደቂቃ ዓሊ ሱሌማን ከግብጠባቂው በረከት ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው ለሀዋሳዎች በጨዋታወረ እጅግ ለጎል የቀረበ አጋጣሚ ሆኖ ጨዋታው አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።