የጨዋታ ሳምንቱ መክፈቻ መርሐግብር በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
መቐለ 70 እንደርታዎች አዳማ ከተማን ካሸነፈው ቋሚ አሰላለፍ ሶፎንያስ ሰይፈ፣ ሸሪፍ መሐመድ እና ኪሩቤል ኃይሉ በምሕረትአብ ገብረህይወት፣ ሰለሞን ሀብቴ እና ያሬድ ከበድ ተክተው ሲገቡ አርባምንጭ ከተማዎች ወላይታ ድቻን ካሸነፈው ቋሚ በፍቅር ቅዛው በፍቃዱ መኮንን ተክተው ገብተዋል።
ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት የመጀመርያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫ የወሰዱበት ነበር። ጥቂት የጠሩ ግብ ሙከራዎች በታየበት አጋማሽ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ አዞዎቹ የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል። ግብ በማስቆጠር ረገድ ቀዳሚ የነበሩት ግን ምዓም አናብስቶቹ ነበሩ፤ በሰባተኛው ደቂቃ ቦና ዓሊ በአርባምንጭ ከተማ ሳጥን በተሰራበት ጥፋት ምክንያት የተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት ያሬድ ብርሀኑ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ በኃላ የተሻለ ብልጫ የነበራቸው እና በአህብዋ ብሪያን እጅግ ለግብ የቀረበች ሙከራ ያደረጉት አዞዎቹም ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላ አቻ የምታደርጋቸው ግብ አስቆጥረዋል። አሕመድ ሑሴን ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለዊ በረዥሙ የለጋው ኳስ የመቐለ 70 እንደርታው ተከላካይ ከጨረፈው በኋላ ሶፈንያስ ሰይፈ ከመያዙ በፊት ዘሎ በግንባር በማስቆጠር ነበር ቡድኑን አቻ ማድረግ የቻለው።
ከግቦቹ መቆጠር በኋላ መቐለ 70 እንደርታ በመድሃኔ ብርሃኔ አርባ ምንጭ ከተማ ደግሞ ካሌብ በየነ ከቆመ ኳስ አሻምቶች አሕመድ ሑሴን በግንባሩ ገጭቶ ሶፎንያስ ሰይፈ በጥሩ ቅልጥፍና በመለሳት ኳስ ዕድሎች ፈጥረዋል። በሰላሣ ሁለተኛው ደቂቃ ላይም መቐለዎች ዳግም ጨዋታውን የሚመሩበት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ያሬድ ብርሀኑ ከተከላካይ ክፍል የተላከችለትን ኳስ በጥሩ መንገድ ሰንጥቋት ቦና ዓሊ በጥሩ መንገድ ወደ ግብ ገፍቶ ከመረብ ጋር የቀላቀላት ኳስም መቐለን መሪ ማድረግ ችላለች።
ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር ሲታይ ደካማ እንቅስቃሴ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረገበት ነበር። ብዙም ማራኪ ባልነበረው አጋማሽ ላይ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በአንፃራዊነት የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው አዞዎቹ በስልሣኛው ደቂቃ ላይ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ የአቻነቷን ግብ አስቆጥረዋል፤ ቻርለስ ሪባኑ ከቀኝ መስመር አሻምቷት ፍቃዱ መኮንን በግሩም ሁኔታ በግንባሩ ያስቆጠራት ኳስም አዞዎቹን ወደ ጨዋታው የመለሰች ግብ ነበረች።
ከአቻነቷ ግብ በኋላ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይህ ነው የሚባል የጠራ የግብ ሙከራ ሳይደረግ ከቆየ በኋላ አዞዎቹ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተሻሉ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። በተለይም ከቀኝ መስመር ተሻምታ አሕመድ ሑሴን ከመታት በኋላ ወደ ቻርለስ ሪባኑ የደረሰች ኳስ ተጫዋቹ መቷት ሶፎንያስ ሰይፈ ያወጣት ሙከራ የማታ ማታ አዞዎቹን አሸናፊ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች። አራት ግቦች ያስመለከተን ጨዋታም በአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።