በ17ኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት የሚከናወኑ መርሐግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!
ወላይታ ድቻ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
የጦና ንቦቹ እና ፈረሰኞቹ ከሽንፈት እና ከአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ ድል ለመመለስ የሚፋለሙበት ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነው።
በሃያ ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች በእስካሁኑ ጨዋታዎቻቸው አምስት ድል፣ አምስት አቻ እና አራት ሽንፈት ገጥሟቸዋል።
ሞቅ ቀዝቀዝ የሚለው አካሄዳቸውም ለነገው ጨዋታ የሚመጡበትን አኳኋን አጠራጣሪ ያደርገዋል።
ከመጨረሻዎቹ ስምንት ጨዋታዎች በአንድ አጋጣሚ ብቻ ድል ማድረግ የቻለው ቡድኑ በተከታታይ ጨዋታዎች ከአቻ ውጤቶች መላቀቅ ባለመቻሉ በደረጃ ሰንጠረዡ እንዲያሽቆለቁል ሆኗል። ለዚህ እንደ ዋነኛ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው ደሞ ቡድኑ ያለበት ውጤትን አስጠብቆ የመውጣት ድክመት ነው። ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት ከአርባምንጭ ከተማ፣ ኢትዮጵያ መድን፣ ሀዋሳ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ጋር ባካሄዳቸው መርሐግብሮች ጨዋታውን መምራት ቢችልም ውጤቱን ማስጠበቅ አልቻለም። አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በነገው ጨምሮ በቀጣይ ጨዋታዎች ይህንን ችግር በቀዳሚነት የመቅረፍ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ከወልዋሎ እና አዳማ ከተማ ቀጥሎ በርከት ያሉ ግቦች (18) ያስተናገደው የመከላከል ጥምረቱ ከመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች በሁለቱም መረቡን ሳያስደፍር መውጣት ቢችልም አሁንም መሻሻል የሚገባው የቡድኑ ክፍል ነው።
ከተከታታይ አራት ድሎች በኋላ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ መጋራታቸውን ተከትሎ ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበት ወርቃማ ዕድል ያባከኑት ፈረሰኞቹ ከአቻ ውጤት ለማገገም የጦና ንቦቹን ይገጥማሉ።
ፈረሰኞቹ ከተከታታይ ድል ወደ ሜዳ በገቡበት የመጨረሻው ጨዋታ የገጠማቸው ፈተና ከብዙዎች ግምት ውጪ ቀላል አልነበረም።
ቡድኑ ምንም እንኳን በጨዋታው ከተጋጣሚው አንፃር ሲታይ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችልም እንደ ወትሮ በርከት ያሉ የግብ ዕድል ባለመፍጠሩ ነጥብ ለመጣል ተገዷል። ግብ በማስቆጠሩ ረገድ እምብዛም ችግር እየታየበት ያልሆነው ቡድኑ በየጊዜው መሻሻል ከታየበት ጥሩ እንቅስቃሴ በዘለለ በጨዋታዎች ያለው የተነሳሽነት ስሜቱ በወጥነት በፉክክሩ እንዲዘልቅ ሊያደርጉት የሚችሉ ነጥቦችን ናቸው። ሆኖም በመጨረሻው ጨዋታ ግብ ለማስቆጠር በነበራቸው የበዛ ጉጉት ከጨዋታ መንገዱ ሲወጡ እና በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ለስህተቶች ሲዳረጉ ተስተውሏል። ከጨዋታው በኋላ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በሰጡት አስተያየት መሰረት በወቅቱ በተጫዋቾቹ የተፈጠረው የመቻኮል ስሜት በነገው ጨዋታ ይኖራል ተብሎ አይገመትም።
በወላይታ ድቻ በኩል አሁንም ባለፉት ተከታታይ ጨዋታ ላይ ጉዳት ምክንያት ቡድኑን እያገለገለ ከማይገኘው ግብ ጠባቂው ቢንያም ገነቱ በስተቀር ሁሉም ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ እንደሚኖሩ ታውቋል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በጉዳት ከሜዳ የራቁት ተከላካዩ አማኑኤል ተርፉ እና አጥቂው ዳግማዊ አርዓያ አሁንም ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆናቸው ሲታወቅ የተቀሩት የፈረሰኞቹ አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች 20 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 9 ወላይታ ድቻ 6 ድሎችን አሳክተዋል። አምስት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ በጨዋታዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ 26 ወላይታ ድቻ ደግሞ 16 ጎሎች አስቆጥረዋል።
ኢትዮጵያ ቡና ከ ባህር ዳር ከተማ
በአራት ነጥቦች እና በአምስት ደረጃዎች የሚበላለጡት ቡናማዎቹ እና የጣና ሞገዶቹ የሚያደርጉት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ የሚገመት ተጠባቂ መርሐግብር ነው።
ከአምስት ሽንፈት አልባ መርሐግብሮች በኋላ በኢትዮጵያ መድን ሽንፈት ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና በአስራ ዘጠኝ ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ቡናማዎቹ ምንም እንኳ ለአምስት ተከታታይ መርሐግብሮች መረባቸውን ሳያስደፍሩ ከዘለቁ በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ በተጫዋቾች የግል ስህተት እና ግብ ማስተናገድ ቢችሉም በሊጉ ጠንካራ የፊት መስመር ካላቸው ክለቦች አንዱ ከሆነው መድን ለ84′ ደቂቃዎች ከፍተኛ ፍልሚያ በማድረግ አሁንም ጠንካራ አደረጃጀት እንዳላቸው አስመስክረዋል። ሆኖም ሊጉ በአዳማ መካሄድ ከጀመረ በኋላ በተከናወኑ ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት መስመራቸው በብዙ ረገድ መሻሻል እንደሚገባው ታይቷል። የግብ ማስቆጠር ችግር የተስተዋለበት ቡድኑ በነገው ዕለትም በሊጉ ጥቂት ግቦች ካስተናገዱ ክለቦች አንዱ የሆነው ቡድን እንደመግጠሙ የአፈጻጸሙን ነገር ነገ አስተካክሎ መቅረብ የግድ ይለዋል።
ከስምንት ሽንፈት አልባ መርሐግብሮች በኋላ በኢትዮጵያ መድን ከገጠማቸው ሽንፈት አገግመው ከመቻል ጋር ነጥብ ተጋርተው የወጡት ባህር ዳር ከተማዎች ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ዳግም ድል ለማድረግ ቡናማዎቹን ይገጥማሉ።
በተከታታይ ትልቅ ግምት ከተሰጣቸው እና በሰንጠረዡ የላይኛው ፉክክር ያሉት ክለቦች የገጠመው ቡድኑ በውድድሩ ዓመቱ ይዞት የዘለቀው ዋነኛ የመከላከል ጥንካሬ ማስቀጠሉ በአወንታዊነቱ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም የግብ ዕድሎችን የመጠቀም ጉልህ ክፍተት ይስተዋልበታል። የጣና ሞገዶቹ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ መሻሻሎች ባሳዩበት ወቅት የገጠማቸው የአፈጻጸም ድክመት ለመቅረፍም
ተጨማሪ ግብ የማግቢያ አማራጮቹ ማስፋት ይጠበቅባቸዋል።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል ጉዳት ላይ ካለው መላኩ አየለ ውጪ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በባህር ዳር ከተማ በኩል ደግሞ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ10 ጊዜያት ተገናኝተው ባህር ዳር ከተማ አራት ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ አንድ ጊዜ ድል ሲያደርጉ አምስቱ ጨዋታዎች አቻ የተጠናቀቁ ናቸው። በግንኙነታቸውም ባህር ዳር ከተማ 18 ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 16 ግቦችን አስቆጥረዋል።