ፈረሰኞቹ በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ታግዘው ወላይታ ድቻን 2-0 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሰዋል።
ወላይታ ድቻ በ16ኛው ሳምንት በአርባምንጭ ከተማ ሽንፈት ካስተናገደው የመጀመሪያ አስራ አንድ ስብስባቸው ስድስት ለውጦችን አድርገው ምንተስኖት ተስፋዬን በኬኔዲ ከበደ፣ ፍፁም ግርማን በውብሸት ክፍሌ ፣ሙሉቀን አዲሱን በአብነት ደምሴ፣ ቴዎድሮስ ታፈሰን በመሳይ ኒኮል፣ ባዬ ገዛኸኝን በካርሎስ ዳምጠው እና ፀጋዬ ብርሃኑን በመሳይ ሰለሞን ተክተው ሲቀርቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ16ኛው ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው የመጀመሪያ አስራ አንዳቸው ባደረጓቸው አራት ለውጦች በአንፃሩ ፍሪምፖንግ ኩዋሜን በአሸናፊ ጌታቸው፣ ሻሂዱ ሙስጠፋን በቶሎሳ ንጉሴ፣ አብዱ ሳሚዮን በአብዱልሀፊዝ ቶፊቅ እና ተገኑ ተሾመን በአማኑኤል ኤርቦ ተክተው ቀርበዋል።
ጨዋታው ገና ከመጀመሩ በመጀመሪያ ደቂቃ ላይ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለን ኳስ አማኑኤል ኤርቦ አግኝቶ ባመከነው አጋጣሚ የጀመረው አጋማሹ በግቦች የሚታጀብ ቢመስልም የኋላ ኋላ ሁለቱም ቡድኖች ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በመጫወታቸው እምብዛም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አላስመለከተንም።
በአጋማሹ ፈረሰኞቸ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ወደፊት እየሄዱ የግብ አጋጣሚ ለመፍጠር ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ደርሰው የወላይታ ዲቻዎችን ተከላካይ መስመር የፈተነ ሙከራ ሲያደርጉ መመለከት አልቻልንም።
ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ በፈጣን ሽግግር የሚያገኙትን አጋጣሚ ወደ ግብ ለመቀየር በረጃጅም ኳሶች ወደፊት ሲገሰግሱ መመለከት የቻልን ቢሆንም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው 30 ደቂቃን የተሻገረ ሲሆን በ31ኛው ደቂቃ ከቆመ ኳስ በተሻማ ኳስ ካርሎስ ዳምጠው ጨርፏት የፈረሰኞቹ ተከላካይ እና ግብ ጠባቂ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት መሳይ ሰለሞን ብቻውን ሆኖ ኳሷን አግኝቶ ወደግብ የሞከራት እና ለጥቂት በግቡ ቋሚ ብረት በኩል ያለፈባቸው ሙከራ በአጋማሹ ቀዳሚ ሊያደርጋቸው የቀረበ አጋጣሚ ነበር።
በሁለተኛ አጋማሽ ጠንከር ብለው የተመለሱት ፈረሰኞቹ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጫን ብለው ወደፊት በመግባት ብልጫ ወስደው የተጋጣሚያቸውን ግብ ክልል ሲጎበኙ አስተውለናል።
ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ መድረሻቸው ካርሎስ ዳምጠውን እና መሳይ ሰለሞንን ባደረጉ ረጃጅም ኳሶች ለውጥ ለመፍጥር ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው ፍሬ ሳያፈራ ጨዋታው ሰባኛውን ደቂቃ ተሻግሯል።
ግቦችን ለማስቆጠር የፊት መስመራቸው ላይ ለውጥ ያደረጉት ፈረሰኞቹ ተቀይረው ሜዳ የገቡ ተጫዋቾች ባደረጉት ጥረት ቀዳሚ መሆኑ የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል።
77ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ተገኑ ተሾመ በቀኝ መስመር በኩል ኳስ ይዞ ወደ ሳጥን በመግባት ያሻማውን ኳስ ሌላኛው ተቀይሮ የገባው አብዱ ሳሚዮ ወደ ግብነት ቀይሮ መሪ አድርጓቸዋል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ወላይታ ድቻዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ በመልሶ ማጥቃት ወደፊት ለመሄድ ጥረት ቢያደርጉም ተጨማሪ ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል።
በፈጣኝ ሽግግር ወደፊት መሄዳቸውን የቀጠሉት ፈረሰኞቹ መሪነታቸውን ማስፋት የቻሉበትን ተጨማሪ ግብ በአማኑኤል ኤርቦ አማካኝነት አግኝተዋል ፤ 85ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ ተገኑ ተሾመ አግኝቶ ብቻውን ተመቻችቶ ሲጠባብቅ ለነበረው አማኑኤል ኤርቦ ያሻገረለትን ኳስ አማኑኤል በግሩም አጨራረስ መረብ ላይ አሳርፏታል።
ጨዋታው ወደ መገባደጃው ሲቃረብ ወላይታ ድቻዎች በተደጋጋሚ ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል በመድረስ ግቦችን ለማስቆጠር በጫና ጥረት ሲያደርጉ ያስተዋልን ቢሆንም ፈረሰኞቹ በጠጣር የመከላከል መዋቅር መሪነታቸውን አስጠብቀው ጨዋታውን 2-0 በሆነ ውጤት በመርታት ወደ ድል ተመልሰዋል።