በጨዋታ ሳምንቱ መገባደጃ ዕለት የሚካሄዱ ተጠባቂ መርሐግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!
ሀዲያ ሆሳዕና ከ መድን
የጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ እና በጉጉት የሚጠበቅ ፍልሚያ እንሚደረግበት የሚጠበቀው ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነው።
ለስድስት የጨዋታ ሳምንታት ተከታታይ ድሎች አስመዝቦ ሊጉን እስከመምራት ደረጃ ደርሶ የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና ከነበረው እጅግ ውጤታማ ጉዞ አንጻር ሲታይ ባለፉት ጨዋታዎች መጠነኛ መደነቃቀፍ ገጥሞታል። በመጨረሻው ሳምንት ከብዙዎች ግምት ውጭ በወልዋሎ ሽንፈት ያስተናገደው ቡድኑ
ካጋጠመው አሉታዊ ውጤት በመውጣት ከሊጉ መሪ በነጥብ ለመስተካከል በነገው ተጠባቂ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ያስፈልገዋል።
ከተከታታይ ድሎች መልስ መቻልን በማሸነፍ የአዳማ ቆይታውን አሃዱ ብሎ የጀመረው ቡድኑ ጦሩን ባሸነፈበት ጨዋታ ያሳየው ብቃት ካቆመበት የቀጠለ አስመስሎት ነበር። ቀጥለው በተካሄዱ ጨዋታዎች ግን በፋሲል ከነማ እና ወልዋሎ ተፈትኖ አምስት ነጥቦችን ጥሏል። ይህ ቢሆንም ግን አሁንም ከመሪዎቹ ጎራ ከመሆን ያገደው አይደለም። ሆኖም ቡድኑ በፉክክር ለመዝለቅ እና ደረጃውን ለማሻሻል ከድንገተኛው ሽንፈት በኋላ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዳለበት ይታሰባል። ለዚህ ደግሞ ከበላዩ የተቀመጠውን ክለብ ማግኘቱ ምላሹን አዎንታዊ የማድረግ ዕድል በእጁ ይገኛል። በዚህም በነገው ጨዋታ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኮስተር ብሎ ወደ ጨዋታው እንደሚቀርብ ይገመታል።
በሃያ ዘጠኝ ነጥቦች በሊጉ መሪነት የተሰየመው ኢትዮጵያ መድን ያለፉትን አምስት ጨዋታዎች ጣፋጭ ድሎች እየተጎናጸፈ በአልቀመስ ባይነቱ ቀጥሏል።
ኢትዮጵያ መድን በሊጉ በአንድ ጨዋታ ብቻ ተረትቶ ዝቅተኛ የሽንፈት መጠን ያስመዘገበ ክለብ ነው። በአዳማ ከተማ ባደረጋቸውን አምስት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ በመሰብስበብ በጥሩ ግስጋሴ ላይ የሚገኘው ቡድኑ የያዘውን የአሸናፊነት ጉዞ ለማስቀጠል እና የሊጉ መሪ ሆኖ ለመዝለቅ ነገ የሚጠብቀውን ፈተና ማለፍ ይጠበቅበታል።
አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በአመዛኙ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት የሚሞክር ቡድን ቢገነቡም በቀጥተኛም እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችም የሚፈጥሩ ተጫዋቾች መያዛቸው ቡድኑ እንዳይገመት አድርጎታል። ቡድኑ በሁሉም የጨዋታ ሂደቶች የሚታዩት ቡድናዊ እንቅስቃሴዎች ውጤት እያስገኘለት እንደሆነ በጉልህ ተስተውሏል፤ ነገም ይህ ባህሪ ከተደገመ ሀዲያ ፈተና እንደሚበዛበት ይገመታል። ከሁሉም በላይ ግን የቡድኑ ያልሸነፍ ባይነት ባህሪ በጨዋታው ትልቅ ግምት እንዲሰጠው ያደርገዋል።
በሀዲያ ሆሳዕና በኩል በረከት ወንድሙ እና መለሰ ሚሻሞ አሁንም በጉዳት በነገው ጨዋታ የማይኖሩ ሲሆን ዳግም ንጉሤም ወደ ልምምድ ቢመለስም የመሰለፉ ነገር ነገ የሚወሰን ይሆናል። የተቀሩት የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በኢትዮጵያ መድን በኩል አዲስ የተሰማ የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን ጉዳት ላይ የሰነበቱት ዮሐንስ ሴጌቦ እና አብዲሳ ጀማል አሁንም ከነገው የጨዋታ ዕለት ስብስብ ውጭ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አራት ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ኢትዮጵያ መድን ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሀዲያ ሆሳዕና በአንድ ጨዋታ አሸንፎ የተቀረው በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር። ስድስት ግቦች በተቆጠሩበት ግንኙነት ሁለቱም ቡድኖች በእኩሌታ ሦስት ሦስት ግቦችን አስቆጥረዋል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ
በአዳማ ከተማ ድል ማድረግ ያልቻሉት እና ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ ማግኘት የተሳናቸው ድሬዳዋ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ወደ ውጤት ለመመለስ ዕድል የሚሰጣቸውን ጨዋታ እርስ በእርስ ያደርጋሉ።
ድሬዳዋ ከተማ አስራ ዘጠኝ ነጥቦች ሰብስቦ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻለው ቡድኑ በመጨረሻው ጨዋታ ከተከታታይ አራት የአቻ ውጤቶች በኋላ ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ በነገው ጨዋታ አሸንፎ የመውጣት ጫናው እንዲያጋድልበት የሚያደርግ ነው።
በድል፣ አቻ እና ሽንፈት መሃል እየተመላለስ ወጥነት በሌለው መንገድ ውድድሩን እየከወነ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ በእንቅስቃሴ ረገድ ሲታይ መጥፎ የሚባል ብቃት ባያሳይም ቀጣይነት ያለው ውጤት የማስመዝገብ ችግር ይስተዋልበታል። እስከ ቅርብ ሳምንታት ድረስ ከመቻል ቀጥሎ በርካታ ግቦች በማስቆጠር በ2ኛ ደረጃነት የነበረው ቡድኑ በአሁኑ ወቅት የቀደመ ጥንካሬውን አጥቶ በተከታታይ ሳምንታት ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኖታል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩ እንዲሁም ኳስ እና መረብ ካገናኘ ሦስት መርሐግብሮች መቆጠራቸውም የዚህ ማሳያ ነው።
ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ ያለው ጥንካሬም ከሌላው የተሻለ ሆኖ እናገኘዋለን፤ ከባለፉት አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ መረቡን ሳያስደፍር መውጣቱም የጥንካሬው አንድ ማሳያ ነው።
ላለፉት አራት የጨዋታ ሳምንታት ድል ማድረግ ያልቻለው ፋሲል ከነማ በበኩሉ በአስራ ሰባት ነጥቦች በወራጅ ቀጠናው አፋፍ የሚገኝ ሲሆን ከአደጋው ቀጠና ለመራቅ የነገው ውጤት ያስፈልገዋል።
በዐፄዎቹ በኩል ጨዋታን በአቻ ውጤት የማጠናቀቅ ጉዳይ ዋና ፈተናቸው ይመስላል። በሊጉ በስምንት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቶ በመውጣት ቀዳሚ የሆነው ክለቡ ድሬዳዋን በተከታታይ ድሎች ቢሰናበትም በአዳማ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ሦስት አቻ እና አንድ ሽንፈት አስተናግዷል። በተጠቀሱት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ሁለት ነጥብ ሦስቱን ብቻ ያሳካው ፋሲል ካለበት የስጋት ቀጠና ለመራቅ እና ከአቻ ውጤቶች ለመላቀቅ የአሸናፊነት መንፈሱን ይበልጥ ማሳደግ እንዳለበት ይጠቁማል።
ቡድኑ ምንም እንኳ በመጨረሻዎቹ ሦስት መርሐግብሮች ጠንካራ ቡድኖችን መግጠሙ ከድል ለመራቁ እንደ አንድ ምክንያት የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም በቀጣይ በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ያሉበትን ድክመቶች መቅረፍ ቀዳሚ ሥራው መሆን ይገባዋል።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል መሐመድኑር ናስር እና ያሬድ ታደሰ በጉዳት አላዛር ማረነ ደግሞ በቅጣት ምክንያት የነገው ጨዋታ ያመልጣቸዋል። በፋሲል ከነማ በኩል ዮናታን ፍስሐ ፣ ኪሩቤል ዳኜ ፣ በረከት ግዛው ፣ ቢኒያም ላንቃሞ እና ተመስገን ካስትሮ አሁንም ጉዳት ላይ በመሆናቸው ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።
ፋሲል እና ድሬዳዋ በሊጉ እስካሁን 14 ጊዜ ተገናኝተዋል። ድሬዳዋ ከተማ በስድስት ጨዋታዎች ድል በማድረግ ቀዳሚ ሲሆን ፋሲል ከነማ አምስት ድሎችን አሳክቶ በቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ 33 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን ፋሲል ከነማ 19 ፤ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 14 ጎሎች አስመዝግበዋል።