ስሑል ሽረ የስነምግባር ጥሰት ፈጽሟል ያለውን ተጫዋች ማሰናበቱን ሲገልፅ ተጫዋቹም ለፌዴሬሽኑ አቤቱታውን አቅርቧል።
ስሑል ሽረዎች የስነምግባር ጥሰት ፈፅሟል ያሉትን የዊልያም ሰለሞን ውል መሰረዛቸውን ገልጸዋል። ለፌዴሬሽኑ በላኩት ደብዳቤ ተጫዋቹ ከፍተኛ የስነምግባር ጥሰት ማሳየቱን በመጥቀስ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ተደጋጋሚ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደሰጡት የገለጹት ሽረዎች ተጫዋቹ የሠራቸውን ግድፈቶች መነሻ በማድረግ የወሰኑትን የስንብት ውሳኔ ፌዴሬሽኑ እንዲያፀድቅላቸው ጥያቄ አቅርበዋል። ተጫዋቹ በበኩሉ ክለቡ ያዘጋጀው መተዳደርያ ደንብ የሌለው መሆኑ እንዲሁም ተሻሽሎ የወጣው የዲስፕሊን መመርያ አንቀፅ 80 ተራ ቁ 26 በማጣቀስ ክለቡ ለብቻ ይህንን ውሳኔ ማስተላለፉ ተገቢ እንዳልሆነ ገልፆ ፌዴሬሽኑ ወደ ሥራው እንዲመልሰው በደብዳቤ ጠይቋል።
ከስሑል ሽረ ጋር የተያያዘ ሌላ ዜና ቡድኑ ላለፉት ወራት ከክለቡ ጋር ቆይታ ከነበራቸው አዲስ ግርማ እና ዮሴፍ ኃይሉ ጋር በስምምነት መለያየቱን ለማወቅ ተችሏል።