ብርቱካን ገብረክርስቶስ ራስዋን ከብሔራዊ ቡድን አገለለች

👉 “ለወጣት ተጫዋቾች ዕድል ለመስጠት ይህንን ወስኛለሁ።”

👉 “በብሔራዊ ቡድን ቆይታዬ ላሰለጠኑኝ አሰልጣኞች አብረውኝ ለተጫወቱ ተጫዋቾች እና በእግር ኳስ ሕይወቴ አስተዋጽኦ ላደረጉት በሙሉ ላቅ ያለ አክብሮት አለኝ።”

በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ስማቸው በጉልህ ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች አንዷ የሆነችው ብርቱካን ገብረክርስቶስ ራስዋን ከብሔራዊ ቡድን አግልላለች።

በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ከታዩ ድንቅ ተጫዋቾች አንዷ የሆነችው ብርቱካን ገብረክርስቶስ ዛሬ ራሷን ከብሔራዊ ቡድን ማግለሏን ገልፃለች። በኤግልስ ፣ አዲስ ኮከብ ፣ ደደቢት፣ ዳሽን ቢራ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨምሮ ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት በእግር ኳሱ ያለችው አንጋፋዋ ተጫዋች በሴቶች እግር ኳስ በጉልህ ስማቸው ከሚጠቀሱ ስመ ጥር ተጫዋቾች አንዷ ናት።

በኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ቆይታዋ ስኬታማ ጊዜን ያሳለፈችው ብርቱካን ከብሔራዊ ቡድኑ ማግለሏን አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገችው አጭር ቆይታ ለሀገሯ ባበረከተችው አስተዋጽኦ እና በቡድኑ በነበራት ቆይታ እጅግ ደስተኛ መሆኗን በመግለፅ ለወጣት ተጫዋቾች ዕድል ለመስጠት ይህንን ውሳኔ መወሰኗ ገልፃለች።

ተጫዋቿ ጨምራም በብሔራዊ ቡድን ቆይታዋ ላሰለጠኗት አሰልጣኞች ፣ አብረዋት ለተጫወቱ ተጫዋቾች እና በእግር ኳስ ሕይወቷ አስተዋጽኦ ላደረጉት በሙሉ እንዲሁም ከጎኗ ላልተለዩ ደጋፊዎች ያላትን ላቅ ያለ አክብሮት ገልፃለች።