በምሽቱ መርሐግብር ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ድሬዳዋ ከተማ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።
ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ17ኛው የጨዋታ ሳምንት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ ተጋርተው ከወጡበት ቋሚ ስብስባቸው ሁለት ለውጦችን በማድረግ ዮናስ ገረመውን እና ዳዋ ሆቴሳን አሳርፈው ሰለሞን ገመቹን እና ናትናኤል ሰለሞንን ይዘው ሲቀርቡ ድሬዳዋ ከተማ በበኩላቸው በ17ኛው ሳምንት በፋሲል ከነማ 2ለ1 በተሸነፉበት ጨዋታ ላይ ከተጠቀሙት ቋሚ ስብስብ ሦስት ለውጦችን በማድረግ ድልአዲስ ገብሬን፣ ሆኖክ ሀሰንን እና ሱራፌል ጌታቸውን አሳርፈው በምትካቸው ተመስገን ደረሰ ፣አቤል አሰበ እና አቡበከር ሻሚልን ተክተው ገብተዋል።
በዋና ዳኛ ባሕሩ ተካ መሪነት ጥንቃቄ በተሞላበት አጀማመር ጅማሮውን ያደረገው የምሽቱ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች እምብዛም የግብ ማግባት እንቅስቃሴ ማስመልከት አልቻለም። ድሬዳዋ ከተማዎች ኳስ ተቆጣጥረው በእርጋታ ወደፊት እየሄዱ ቀዳሚ ለመሆን ሲጥሩ ወልዋሎዎች በበኩላቸው በረጃጅም ኳሶች ወደ ተቀራኒ ቡድን ግብ ክልል ሲደርሱ ተስተውለዋል። ሆኖም ግን ሁለቱም ቡድኖች አስቆጪ የሚባል አጋጣሚ መፍጠር ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው የአጋማሹ አካፋይ ላይ ሲደርስ ቢጫዎቹ ጎል ማግኘት ችለዋል። በ22ኛው ደቂቃ ላይ ከተከላካይ ጀርባ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ ናትናኤል ሰለሞን ፍጥነቱን ተጠቅሞ ደርሶ ከግብ ጠባቂው ዐብዩ ካሣዬ ጋር ተገናኝቶ ዘሎ ኳሷን በማሻገር ብቻውን ሆኖ ሳጥን ውስጥ በመግባት በቀላሉ መረብ ላይ አሳርፎ ቢጫዎቹን ቀዳሚ አድርጓቸዋል።
በመስመር በኩል ሰብሮ መግባቱን ዋና አማራጭ ያደረገው የብርቱካናማዎቹ አጨዋወት በአመዛኙ በቀኝ መስመር በኩል ኳሶችን ይዘው በመግባት ጥቃት ለመሰንዘር ሲጥር ያስተዋልን ቢሆንም ይዘዋቸው የሚገቡትን ኳሶች በመጠቀሙ ረገድ ደካማ ሆነው አምሽተዋል። ወልዋሎዎች በበኩላቸው ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ወደ ኋላ ያፈግፍጉ እንጂ በረጃጅም ኳሶች ወደ ሦስተኛው ሜዳ ክፍል አልፈው አልፈው ሲደርሱ አስተውለናል።
ድሬዳዋ ከተማዎች የኳስ ቅብብል ብልጫ ወስደው ባመሹበት በአጋማሹ ምንም እንኳን የኳስ ንክኪ የበላይነት ቢያሳዩም ጠንከር ያለ የግብ ማግባት እንቀስቃሴ ሳያስመለክቱ ቆይተው ጨዋታው 42ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ አደገኛ ሙከራ አድርገዋል፤ ከቢጫዎች ተከላካዮች ተጨራርፋ የወጣችው ኳስ መስዑድ መሐመድ ጋር ደርሳ ጠንክር ያለ ሙከራ ወደ ግብ መትቶ ከግብ አግዳሚ ለትንሽ ከፍ ብላ ያለፈችበት አጋጣሚ ሲታወስ አጋማሹ ሊጠናቀቅ አካባቢ ጫን ብለው ትኩረታቸውን ሙሉ በሙሉ ማጥቃቱ ላይ አድርገው አቻ ለመሆን ወደ ተጋጣሚዎቻቸው ግብ ክልል ደርሰው አደጋዎችን ለመፍጠር ጥረት ያድርጉ እንጂ ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸው አጋማሹ ተገባዷል።
ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ብርቱካናማዎቹ ሁለት የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ገብተው ሙሉ ኃይላቸውን ተጠቅመው ጥቃት መሰንዘራቸው ቀጥለዋል። ቢጫዎቹ በአንፃራዊነት መከላከሉን ዋና ትኩረት አድርገው ኳሶችን በማራቅ ላይ ቢጠመዱም ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ረጃጅም ኳሶችን ከተከላካይ ጅርባ በመጣል ሌላ ጎል ለማግባት ሲጥሩ ተመልክተናል። በ53ኛው ደቂቃ ላይ የቆመ ኳስ መስዑድ መሐመድ አቃብሎት አብዱሰላም የሱፍ አክርሮ ወደ ግብ መጥቶ በረከት አማረ እንዴትም አውጥቶባቸዋል።
የአቻነት ግብ ፍለጋ ሙሉ ትኩረታቸውን መጣቃቱ ላይ አድርገው በተደጋጋሚ የተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ሲደርሱ የነበሩት ብርቱካናማዎቹ በአጋማሹ የጥረታቸው ፍሬ የሆነችዋን ግብ ለማስቆጠር እስከ 75ኛው ደቂቃ ድረስ መጠበቅ ግድ ሆኖባቸው ቆይተው በመጨረሻም ኳስና መረብ ማገናኘት ችለዋል። ተቀይሮ ሜዳ የገባው ሱራፌል ጌታቸው በጥሩ ሁኔታ ያሻገረውን ኳስ አስራት ቱንጆ አግኝቶ ግብ ጠባቂውን አታሎ በማለፍ ግሩም ግብ መረብ ላይ አሳርፎ ብርቱካናማዎችን ወደ ጨዋታ መልሷቸዋል።
ጎሉ ያነቃቃቸው ብርቱካናማዎቹ ወደፊት መሄዳቸውን ቀጥለው በ79ኛው ደቂቃ ላይ በረከት አማረ ኳስ አስቀምጦ ድጋሚ ሁለት የኳስ ንክኪ አድርጓል በሚል ሁለተኛ ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ አግኝተው ሳይጠቀሙ የቀሩበት ክስተት ይጠቀሳል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ብርቱካናማዎቹ ከአንድ ነጥብ ይልቅ ሦስት ነጥብ በመምረጥ በርከት ብለው ወደ ተጋጣሚው ግብ ክልል እየደረሱ የግብ ማግባት እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ጥራት ያለውን ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ቢጫዎቹ በበኩላቸው ተጨማሪ ግብ ላለማስተናገድ ከራሳቸው ሜዳ ክፍል ኳስ ሲያርቁ ተመልክተናል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክት 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞቹ አስተያየት ያጋሩ ሲሆን አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ቡድን ላይ ጭንቀት አለ ጭንቀት ያመጣው ነገር ነው እንጂ ውጤት ይዘን መውጣት እንችል ነበር ፤ በተጫዋቾቼ ላይ የልምድ እጥረት ጎልቶ ይታያል የሚል አስተያየት ሲሰጡ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው የቻልነውን ያክል አድርገናል ግን አቻ ዛሬ አይገባንም ነበር፤ እንደቡድን መሻሻሎች ያስፈልጉናል፤ አራት ወራጅ ቡድን በመኖሩ 20 ነጥብ መያዛችን መጥፎ አይደለም የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።