የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ሳምንታት በየትኛው ከተማ እንደሚካሄድ ታውቋል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቀጣይ የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያዎቹ የጨዋታ ሳምንታት ጨዋታዎች በየትኛው ከተማ እንደሚካሄድ የሊጉ አክሲዮን ማኀበር ወስኗል።

የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ከአስራ ሁለተኛው ሳምንት አንስቶ በአዳማ ከተማ ሲካሄድ ቆይቶ የካቲት ሦስት የመጀመርያው የውድድር አጋማሽ ፍፃሜውን ያገኛል።

በመሃል የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች እና ዕረፍት እንደተደረገ ከየካቲት 20 በኋላ የሊጉ የሁለተኛው ዙር ውድድሮች በየትኛው ከተማ ይካሄዳል የሚለው ሶከር ኢትዮጵያ ከሰሞኑ በሰራችው ዘገባ ፍንጭ መስጠቷ ይታወቃል።

የተለያዩ ምክንያቶችን በማስቀመጥ ሀዋሳ ከተማ የመካሄዱ ዕድል ሰፊ ሊሆን እንደሚችል ነገር ግን የአወዳዳሪው አካል ገምጋሚ አካላት ወደ ሀዋሳ በማቅናት እየተከናወኑ ያሉትን የልምምድ እና የመጫወቻ ሜዳዎች የማሻሻያ ስራዎችን ምልከታዎችን በማድረግ የመጨረሻ የማረጋገጫ ውሳኔ በቅርቡ እንደሚሰጡ ጠቁመን ነበር።

ሆኖም የሊጉ አክሲዮን ስራ አመራር ቦርድ ባደረገው ስብሰባ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ውድድሩ ወደ ሀዋሳ የመሄዱን ነገር ያመነበት ቢሆንም ሁለተኛው ዙር ከጀመረ ከሦስት ሳምንት በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለበት ሁለት የማጣርያ ጨዋታ ምክንያት ተመልሶ ውድድሩ መቋረጡ ሰለማይቀር ሀዋሳ ሄዶ ከማቋረጥ ይልቅ ለተጨማሪ ሳምንታት በአዳማ መቆየት አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ውድድሩ በአዳማ ከተማ ከየካቲት 20 ጀምሮ ለሦስት ሳምንት ለማድረግ መወሰኑን ሰምተናል።

ባሳለፍነው ሰኞ ክለቦች ቁጥር 18 መሆኑ እንዲሁም ተስተካካይ ጨዋታችን ለማስቀረት ሲባል የ2ተኛውን ዙር አዲስ ድልድል የተደረገ ሲሆን ሰዓት እና ቀኑ ጨምሮ ዛሬ መርሐ-ግብር ይፋ ይሆናል።