ሪፖርት | የጦና ንቦቹ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል

ወላይታ ድቻዎች በካርሎስ ዳምጠው ብቸኛ ግብ መቐለ 70 እንደርታን 1ለ0 በማሸነፍ ወደ ድል ሲመለሱ ምዓም አናብስት በአዳማ ቆይታቸው የመጀመሪያ ሽንፈት ቀምሰዋል።

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታ እና ወላይታ ድቻ ተገናኝተው ምዓም አናብስት በ17ኛ ሳምንት ከአርባምንጭ ጋር 2-2 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ሰለሞን ሀብቴን አስወጥተው ሸሪፍ መሐመድን ሲያስገቡ የጦና ንቦቹ በአንጻሩ በተመሳሳይ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ 2ለ0 ከተሸነፉበት አሰላለፍ አብነት ሀብቴ ፣ ናትናኤል ናሴሮ ፣ መሳይ ኒኮል እና ያሬድ ዳርዛን አሳርፈው ቢኒያም ገነቱ ፣ ፍጹም ግርማ ፣ ቴዎድሮስ ታፈሰ እና ጸጋዬ አበራን አስገብተዋል።

9 ሰዓት ላይ በዋና ዳኛ መስፍን ዳኜ መሪነት የተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ እጅግ ቀዝቃዛ ነበር። ከአንድ ቡድን ስር ረዙም ላሉ ደቂቃዎች የኳስ ቅብብል ባልተደረገበት ጨዋታ 4ኛ ደቂቃ ላይ የድቻው ፍጹም ግርማ ካደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ በኋላ መቐለዎች ባልታሰበ አጋጣሚ ጎል ሊያገኙ ነበር። 15ኛ ደቂቃ ላይ ተከላካዩ  ሸሪፍ መሐመድ ከረጅም ርቀት የመታው ኳስ ነጥሮ ግብ ሊሆን ሲል ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ እንደምንም አስወጥቶታል።

ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ባልታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ የተሻለ የሚባለው የግብ ዕድል 27ኛ ደቂቃ ላይ በወላይታ ድቻዎች አማካኝነት ተፈጥሮ ቴዎድሮስ ታፈሰ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ካርሎስ ዳምጠው ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታውም እጅግ አሰልቺ እየሆነ ቀጥሎ አጋማሹም ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ መቐለዎች ቦና ዓሊን አስወጥተው ብሩክ ሙሉጌታን በማስገባት ጥሩ አጀማመር ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም በማጥቃት እንቅስቃሴው ላይ ግን ሁለቱም ቡድኖች እንደተቀዛቀዙ ጨዋታው ቀጥሎ ድቻዎች ብሥራት በቀለን በመሳይ ሰለሞን ፤ መቐለዎች ኪሩቤል ኃይሉን በሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ቀይረው በማስገባት ጨዋታቸውን ለማሻሻል ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል።

ቀዝቃዛውን ጨዋታ ነፍስ የዘራበት ጎል 73ኛ ደቂቃ ላይ ተገኝቷል። ጸጋዬ ብርሃኑ ከቀኝ መስመር ወደ መሃል ቀንሶ ያመቻቸውን ኳስ ያገኘው ኬኔዲ ከበደ ኳሱን ወደ ሳጥን ውስጥ ልኮት በመቐለ በኩል ተቀይሮ የገባው ኪሩቤል ኃይሉ በገባበት ቅጽበት ኳሱን ከነካው በኋላ ያገኘው ካርሎስ ዳምጠው ግብ አስቆጥሮ የጦና ንቦቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

ጎል ከተቆጠረ በኋላ በተነቃቃው ጨዋታ ድቻዎች 81ኛው ደቂቃ ላይም እጅግ ያለቀለት የግብ ዕድል ፈጥረው ጸጋዬ ብርሃኑ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ካርሎስ ዳምጠው ሳያገኘው ሲቀር ብሥራት በቀለም ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል። ይህም የተሻለው የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው በወላይታ ድቻ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የመቐለ 70 እንደርታው አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ጨዋታው ባሰቡት መንገድ እንዳልሄደ በተለይም መሃል ላይ መቀዛቀዞች እንደነበሩ ጠቅሰው በማጥቃት እንቅስቃሴው ችኮላዎች እንደነበሩ ሲናገሩ የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በበኩላቸው ጠንካራ ጨዋታ እንደነበር ጠቁመው በአጨራረሱ ላይ ችግር እንደነበር በመናገር እንደምክንያትም የሜዳውን ኳስ የማንጠር ጸባይ ጠቅሰዋል። አሰልጣኙ አክለውም የወጣው የፋይናንስ ስርዓት ትልልቅ ተጫዋቾች በአንድ ቡድን እንዳይከማቹ በማድረጉ በሊጉ ጠንካራ ፉክክር እንዲፈጠር ምክንያት እንደሆነ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።