ሪፖርት | አዝናኙ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

ግማሽ ደርዘን ጎሎች የተቆጠሩበት እና በድራማዊ  ክስተቶች የታጀበው የአዞዎቹ እና የነብሮቹ ጨዋታ 3ለ3 ተቋጭቷል።

አርባምንጭ ከተማዎች በ17ኛው ጨዋታ ሳምንት ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ነጥብ ተጋርተው ከወጡበት ጨዋታ የሁሉት ተጫዋች ቅያሪ አድርገው ካሌብ በየነን እና አህመድ ሁሴንን በጉዳት ምክንያት አሳርፈው አንዱዓለም አስናቀን እና አስቻለው ስሜን ይዘው ሲቀርቡ ሀዲያ ሆሳዕናዎች በ17ኛው ሳምንት በኢትዮጵያ መድን ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታ ላይ ከተጠቀሙት አሰላለፍ አራት ለውጦችን በማድረግ በረከት ወልደዮሐንስን፣ ቃለአብ ውብሸትን፣ ሰመረ ሀፍተይን እና ብሩክ በየነን በማሳረፍ ዳግም ንጉሴን ፣ አስጨናቂ ፀጋዬን ፣*ፀጋአብ ግዛውን እና ጫላ ተሺታን ይዘው ቀርበዋል።

ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ በነበረው ጨዋታ ነብሮቹ የመጀመሪያ በለጋ ጨዋታ እድሜ ጎል አስቆጥረዋል ፤ የቆመ ኳስ ሄኖክ አርፊጮ ቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ግብ ላይ አክሎ ነብሮቹ ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ጨዋታው በአርባምንጭ ከተማዎች ቁጥጥር ስር ሆኖ ይቀጥል እንጂ ነብሮቹ ተጨማሪ ግብ ሳይታሰብ አስቆጥረው ጨዋታው ገና በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ላይ እያለ ሌላኛውን ግብ አግኝተው ጨዋታውን ወደ መጨረስ ተቃርበዋል፣ በ14ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ዳግም ንጉሴ በግንባሩ ገጭቶ መረብ ላይ በማሳረፍ የነብሮቹን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጎ ጨዋታውን ወደመጨረስ አቅርቧቸዋል።

ምንም እንኳን ሁለት ግቦችን ቢያስተናግዱም በንክኪ ብልጫዎችን የወሰዱት አዞዎቹ ጨዋታው 24ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ብሩክ ባይሳ ላይ የሀድያ ሆሳዕና ተካላካዮች በፈፀሙት ጥፋት መነሻነት ፍፁም ቅጣት ምት  ተሰጥቷቸው አህቡዋ ብሪያን አምክኖታል። በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብ ፍለጋቸውን የቀጠሉት ነብሮቹ በ34ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ የቆመ ኳስ አግኝተው ሆኖክ አርፍጭ ወደ ግብ ቢመታም የግቡ አግዳሚ ተጨርፋ ወደ ውጪ ወጥታበታለች።

የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሴከንዶች ሲቀሩት አርባምንጭ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያስቻላቸውን ግብ መረብ ላይ አክለዋል፤ ከመሀል ሜዳ አከባቢ የተሻማውን ኳስ ቡታቃ ሸመና በደረቱ አቁሞ ዞሮ በመምታት በግሩም ሁኔታ መረብ ላይ አሳርፎ ቢያንስ ወደ ጨዋታው ተመልሰው ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ አስችሏቸዋል።

ጨዋታው በሁለተኛ አጋማሽ ሲመለስ አዞዎቹ የአቻነት ጥብ ፍለጋ ጠንከር ያሉ ሙከራዎችን በማድረግ ቀጥለው በ59ኛው ደቂቃ ላይ ቻርልስ ሪባኑ በግሩም አንድ ለአንድ ግንኙነት አታሎ በማለፍ ያሻገረውን ኳስ አሕቡዋ ብርያን አግኝቶ ከፍ ሲልበት በድጋሚ በረጅሙ ከተከላካዮች የተጣለውን ኳስ እራሱ አሕቡዋ ብሪያን በፍጥነት ደርሶ ግብ መውጣቱን በሚገባ በመመልከት በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብ በመምታት ከመረብ ጋር አገናኝቶ አቻ አድርጓቸዋል።

አዞዎቹ የአቻነት ግብ አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ከተመለሱ በሴከንዶቹ ልዩነት አሸናፊ ፊዳ በኢዮብ ዓለማየሁ ላይ በፈፀመው ከክንድ መማታት ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተበት ክስተት ተጠቃሽ ነበር ። እንዲሁም በ64ኛው ደቂቃ ላይ የአዞዎቹ ግብ ጠባቂ ኳስ ሁለቴ ንክኪ አድርጓል በሚል ዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ ሁለተኛ ቅጣት ምት ቢሰጡም በድጋሚ የሻሩበት ሌላኛው ክስተት ይጠቀሳል።

ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ እያስመለከተ ጨዋታው ቀጥሎ ሁለቱም ቡድኖች በመልሶ ማጥቃት ግቦች ለማስቆጠር በፈጣን ጨዋታ ሽግግር የግብ ማግባት ጥረት እያደረጉ ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ ሃያ ደቂቃዎች አምርቷል። በአሸናፊ ፊዳ በቀይ ካርድ ከሜዳ መወገዱን ተከትሎ የጨዋታ እንቅስቃሴ የረበሻቸው አዞዎቹ በመልሶ ማጥቃት የግብ ማግባት እድሎችን መፍጠራቸውን አጠንከርው 75ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን የተረከቡበትን ጎል ሳይጠበቅ መረብ ላይ አሳርፈዋል፤ ይሁን እንዳሻው ከቅጣት ምት ከተካላካይ ጀርባ የጣለውን ኳስ ቡታቃ ሸመና በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት መረብ ላይ አሳርፎ አዞዎቹን መሪነቱን እንዲረከቡ አስችሏቸዋል።

ጨዋታው ወደመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ሲያመራ ነብሮቹ በተሻጋሪ ኳሶች ጠንከር ብለው ቢያንስ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ አስተውለናል። ሆኖም ግን በድራማዊ ክስተት ወርቃማ የጨዋታ መሪነት ያገኙት አዞዎቹ ከወገብ በታች ወረድ ብለው በመከላከላቸው እንኳን ግብ ማስቆጠር ጠንከር ያለ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ መፍጠር እየተሳናቸው ይበልጥ መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ መገባደጃ ደርሷል።

ጨዋታው በዚህ ውጤት የሚጠናቀቅ ቢመስልም በይበልጥ ወደ አቻነት ግብ ፍለጋ ትኩረት ያደረጉት ነብሮቹ ጫን ብለው የግብ አጋጣሚዎቹን መፍጠራቸውን ቀጥለው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ነጥብ መጋራት ላይ የደረሱበትን ግብ መረብ ላይ አክለዋል። 89ኛው ደቂቃ ላይ ኢዮብ ዓለማየሁ የቆመ ኳስ ወደ ግብ አሻምቶ ብሩክ ማርቆስ በግንባሩ ገጭቶ መረብ ላይ አክሎ ነብሮቹን አቻ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

የተጫዋች ጉድለትን እንደክፍተት የተጠቀሙት ነብሮቹ ከአንድ ነጥብ ይልቅ ሦስት ነጥብ ፍለጋ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫን ብለው ጥቃት መሰንዘራቸውን በጭማሪ ደቂቃዎች ላይ የቀጠሉ ቢሆንም አጋጣሚውን ወደ ግብነት መቀየር ሳይችሉ ቀርተው ድራማዊ ክስተቶችን ያስመለከተው የነብሮቹ እና የአዞዎቹ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተቋጭቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ያጋሩ ሲሆን አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ “ቀድመን ሁለት ጎሎችን ማስቆጠራችን መዘናጋቶችን ፈጥሮብናል፤ የተከላይ መስመራችን የተደራጅ አይደለም ያን ማስተካከል ይጠበቅብናል፤ ለስህተቶቹ እኔ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ።” ብለዋል። አሰልጣኝ በረከት ደሙ በበኩላቸው እንደቡድን በሠራነው ስህተት ጨዋታውን ሁለት ለባዶ ጀመረናል ግን ጨዋታውን ከመመራት ተነስተን ውጤቱን ወደ መቀበልስ ደርሰናል ፤ ቀይ ካርድ ያስተናገድንበት መንገድ በፍፁም ተገቢ አይደለም ፤ እንደዚህ ከዲሲፕሊን ውጪ የሆኑ ክስተቶችን ከቡድኑ ማስወገድ አለብን። ሁኔታዎችን ስታይ የዛሬው አንድ ነጥብ በቂ ነው።” የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።