የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ በሚደረጉ ተጠባቂ ጨዋታዎች ይቀጥላል፤ ብርቱ ፍልሚያ ይደረግባቸዋል ተብለው የሚጠበቁ መርሀ-ግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ኢትዮጵያ ቡና ከ መቻል
ሁለት የመዲናይቱ አንጋፋ ክለቦች የሚያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሀ-ግብር ነው።
ከነገው ተጋጣሚያቸው በአራት ነጥቦች ዝቅ ብለው በሀያ ሦስት ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በሰንጠረዡ ወገብ ባለው የነጥብ መቀራረብ ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት እስከ ሁለት ደረጃዎች አሻሽሎ ዙሩን የማጠናቀቅ ዕድል አላቸው።
በውድድር ዓመቱ በተከታታይ ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻሉት ቡናማዎቹ በውጤት ረገድ የወጥነት ችግር ይታይባቸዋል።ከኳስ ውጭ ባለው እንቅስቃሴ በሊጉ ፈታኝ ከሆኑ ክለቦች ውስጥ የሚጠቀሰው ቡድኑ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ላይ ካለው ታታሪነት በተጨማሪ በፊት መስመር ላይ የሚጫወቱት ተጫዋቾች ፍጥነት በነገው ጨዋታ ለመቻል አደጋ አምጪ እንደሚሆን ይታመናል። በነገው ወሳኝ ፍልሚያም ጦሩ በአመዛኙ ለኳስ ቁጥጥር ቅድምያ ሰጥቶ ይገባል ተብሎ ስለሚታሰብም ይህንን ከኳስ ውጭ ያለው አዎንታዊ ጎን ያስቀጥላል ተብሎ ይገመታል።
በተጨማሪም በጨዋታ በአማካይ 0.9 ግቦችን ብቻ እያስቆጠረ ያለው ቡድኑ ፊት ላይ ስል መሆን እንደሚጠበቅበት ይታመናል። በተለይ ደግሞ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾቹ የሚያገኟቸውን የግብ ማግባት ዕድሎች መጠቀም ይኖርባቸዋል።
በእንቅስቃሴም ይሁን በውጤት ረገድ በድሬ ያሳዩት ወጥነት ያለው ብቃት በአዳማ መድገም ያልቻሉት መቻሎች በቅርብ ሳምንታት ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ከመሪዎቹ እንዲርቁ አስገድዷቸዋል።
በዘንድሮ የውድድር ዓመት በሊጉ ደረጃ ሰንጠረዥ መሪ ከነበሩ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው መቻል እስከ ቅርብ ሳምንታት ድረስ በሊጉ በማጥቃት ጥንካሬያቸው በቅድምያ ከሚጠቀሱ ክለቦች አንዱ ነበር፤ ለሳምንታት በርቀት የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ክለብ ሆነ የዘለቀው ቡድኑ በቅርቡ ግን ጥንካሬውን አጥቷል። በውድድር ዓመቱ ሀያ ሦስት ግቦችን ያስቆጠረው የማጥቃት ጥምረት በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ ኳስና መረብ ማገናኘቱም አንዱ ማሳያ ነው።
ጦሩ ለገጠመው የውጤት መፋዘዝ ዋነኛ ምክንያት ነው ተብሎ የሚጠቀሰው ደግሞ ይህ ዕድሎችን ወደ ግብነት የመቀየር ድክመት ነው ፤ ውድድሩ ወደ አዳማ ከተማ ከተዘዋወረ ወዲህ በተከናወኑ ስድስት መርሀ-ግብሮች አንድ ድል፣ ሦስት አቻ እና ሁለት ሽንፈት የገጠሙ ቡድኑ በነገው ወሳኝ ጨዋታ የጎል ፊት ችግሩ ቀርፎ ከመጣ አዎንታዊ ውጤት ሊያገኝ እንደሚችል ይታሰባል።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል ሁሉም የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በመቻል በኩል ያለውን መረጃ ለማጣራት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ቡድኑ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ማካተት አልቻልንም።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 34 ጨዋታዎችን አድርገው ኢትዮጵያ ቡና 17 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መቻል 7 ጊዜ ድል አድርጎ በ10 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። ቡናማዎቹ 53 ጦሩ ደግሞ 34 ግቦችን አስቆጥረዋል።
ሀድያ ሆሳዕና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
በመጨረሻው ጨዋታ ነጥብ ተጋተው የወጡት እና ዙሩን በድል ለማገባደድ ወደ ሜዳ የሚገቡት በሁለት ነጥቦች የሚበላለጡ ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።
ለሳምንታት በድሎች ታጅቦ በመዝለቅ ሊጉን እስከ መምራት ደርሶ የነበረው የነብሮቹ ስብስብ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ያስመዘገባቸው ደካማ ውጤቶች ከመሪው በአምስት ነጥቦች ርቆ በ4ኛ ደረጃነት እንዲቀመጥ አስገድደውታል። ቡድኑ በመጨረሻው ጨዋታ ከሁለት ግብ አልባ መርሀ-ግብሮች በኋላ ሦስት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም በተቃራኒው የኋላ መስመሩ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ አፍሳሽ ሆኗል። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ያስተናገደው ቡድኑ በተለይም በመጨረሻው ጨዋታ የነበረው ለስህተቶች ተጋላጭ የሆነ የመከላከል ውቅር ማስተካከል ይኖርበታል።
ከዚህ በተጨማሪም በድራማዊ ክስተቶች ታጅቦ በተካሄደው እና ስድስት ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታ ላይ ቡድኑ ከሁለት ለባዶ መመራት ተነስቶ ነጥብ እንዲጋራ ያስቻለ የአልሸነፍ ባይነት ስሜት በነገው ዕለት መቀጠል የሚገባው ጠንካራ ጎን ነው።
ከመጨረሻዎቹ ሰባት ጨዋታዎች 17 ነጥቦች ያሳኩት ፈረሰኞቹ ነገሮች እንዳሰቡት እየሄዱላቸው ይመስላል። በውድድር ዓመቱ ጥቂት ሽንፈት ከገጠማቸው ክለቦች ተርታ የሚመደበው ቡድኑ ሽንፈት ካስተናገደ ስምንት የጨዋታ ሳምንታት ከማስቆጠሩም ባለፈ በመጨረሻዎቹ መርሀ-ግብሮች ተደጋጋሚ ድሎች በማስመዝገብ ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት ተጠግቷል። ቡድኑ ምንም እንኳን በተጠባቂው የሸገር ደርቢ አቻ ተለያይቶ ሁለት ነጥቦች ለመጣል ቢገደድም በተለይም በአዳማ ቆይታው ጥሩ እንቅስቃሴው በምን መንገድ ወደ ውጤት መመንዘር እንዳለበት በሚገባ ተምሯል። በመጨረሻዎቹ ሰባት ጨዋታዎች አስር ግቦች ያስቆጠረው እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የሚገኘው የማጥቃት ጥምረቱም ለቡድኑ ውጤት ማማር የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።
አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በቅርቡ ያሳኩት ሌላው ትልቁ ነገር የመከላከል አደረጃጀታቸው ጥንካሬ ነው፤ በመጨረሻዎቹ አምስት መርሀ-ግብሮች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደ ጠንካራው የፈረሰኞቹ የኋላ ክፍል ከፈጣኖቹ የነብሮች አጥቂዎች የሚያደርጉት ፍልሚያም ጨዋታውን ተጠባቂ ያደርገዋል።
በሀድያ ሆሳዕና በኩል በረከት ወልደዮሐንስ ከቅጣት ሰመረ ሀፍታይ ደግሞ ከህመም ሲመለሱ በረከት ወንድሙ እና መለሰ ሚሻሞ ግን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይኖሩም። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በጉዳት የሰነበተው ተከላካዩ አማኑኤል ተርፉ አገግሞ ልምምድ ቢጀምርም ለነገው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው።
ቡድኖቹ እስካሁን አስር ጊዜ ተገናኝተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት፤ ሀዲያ ሆሳዕና ሁለት ድሎችን አሳክተው አራት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ አስር ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ አራት ግቦች አስቆጥረዋል።