መረጃዎች | 76ኛ የጨዋታ ቀን

ተጠባቂውን ደርቢ ጨምሮ ቻምፒዮኖቹ እና የጦና ንቦቹ በመጀመርያው ዙር የበላይ ሆኖ ለማጠናቀቅ የሚያደርጓቸው ተጠባቂ መርሐግብሮች በነገው ዕለት ይከናወናሉ።

ባህር ዳር ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

በጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ ከሆኑ ፍልሚያዎች አንዱ የሆነው እና ከዚህ ቀደም በርከት  ያሉ የአቻ ውጤቶች የተመዘገቡበት ደርቢ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነው።

በሃያ ሦስት ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህር ዳር ከተማዎች በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ከራቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ ዐፄዎቹን ይገጥማሉ።

ለስምንት የጨዋታ ሳምንታት ሳይሸነፉ ከዘለቁ በኋላ ከመጨረሻዎቹ ሦስት መርሐግብሮች በሁለቱ ሽንፈት የቀመሱት የጣና ሞገዶቹ በ16ኛው የሊጉ ጨዋታ ላይ ለሳምንታት በጥንካሬው የዘለቀው የመከላከል ውቅራቸው ከባድ ፈተና አስተናግዷል። በጨዋታው በአስራ አምስት መርሐግብሮች ሰባት ግቦች ብቻ ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀት በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ከአንድ ግብ በላይ በማስተናገድ ለፈጣኖቹ የቡናማዎቹ አጥቂዎች እጅ ሰጥቷል።

አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው በነገው ጨዋታ መጠነኛ መንገራገጭ የገጠመውን ጠንካራ የኋላ ክፍል ወደ ቀደመ ጥንካሬው መመለስ ቀዳሚ ሥራቸው ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን እንደ ቡድኑ ውጤት ሁሉ የወጥነት ችግር እየተስተዋለበት ያለው የፊት መስመርም በመጨረሻው ጨዋታ ለፍጹምነት የቀረበ ጥንካሬ ላሳየው የፋሲል ከነማ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት በሚመጥን አኳኋን መቅረብ ይኖርበታል።

ሁለት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግበው በደረጃ ሰንጠረዡ ሽቅብ የወጡት ፋሲል ከነማዎች በዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ሦስት ተከታታይ ድሎች ማስመዝገብ ቢያንስ ሁለት ደረጃዎች አሻሽሎ የመጀመርያውን ዙር የማጠናቀቅ ዕድል ይሰጣቸዋል።

በመጨረሻው ጨዋታ የሊጉን መሪ ማሸነፍ የቻሉት ዐፄዎቹ በዕለቱ የተገበሩት የጨዋታ ዕቅድ በሁሉም ረገድ የተዋጣለት ነበር ማለት ይቻላል። በመጀመርያው አጋማሽ በጥሩ የመከላከል አደረጃጀት የመድንን ጥቃት ማክሸፋቸው ግብ ባስቆጠሩበት ሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ከመከላከሉ ባለፈ በተሻለ መንገድ የግብ ዕድሎች መፍጠራቸው ከወሳኙ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዘው እንዲወጡ አስችሏቸዋል።

ዐፄዎቹ ጥሩ የማጥቃት ጥንካሬ ካላቸው እና በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ካሉት ኢትዮጵያ መድን፣ መቻል፣ ሀድያ ሆሳዕና እና ኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረጓቸው የመጨረሻ አራት ጨዋታዎች ያሳዩት የመከላከል ብርታት ዋነኛው ጠንካራው ጎናቸው ነው። ሆኖም በማጥቃቱ እንዲሁም በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ያላቸው ጥንካሬ አጥጋቢ አይደለም። ቡድኑ በማጥቃቱ ረገድ ፍጥነት አልባ ስልት መከተሉ የተጋጣሚ ተከላካዮች ብዙም እንዳይረበሹ ያደረገ ይመስላል። እርግጥ በቡድኑ ውስጥ ፍጥነት ያላቸው ተጫዋቾች በላይኛው የሜዳ ክፍል ላይ ቢኖሩም መዋቅራዊው የማጥቃት አጨዋወት ግን ዝግ ያለ ነው። በመጨረሻው ጨዋታ የተዋጣለት አቀራረብ የነበራቸው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በነገው ወሳኝ የደርቢ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ለማግኘት በማጥቃት አጨዋወቱ ላይ ውስን ለውጦች ማድረግ ሳይኖርባቸውም አይቀርም።

ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ ብልጫ በወሰደባቸው ጨዋታዎችም ጭምር በጠባብ ውጤቶች መደምደሙ (በውድድር ዓመቱ ድል ያደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች በአንድ የግብ ልዩነት የተጠናቀቁ ናቸው) እና ውጤት ለማስጠበቅ ጫና ውስጥ ሲገባ የታየባቸው ቅፅበቶች መኖራቸው ሲታይ የአፈፃፀም ደረጃው ከፍ ማድረግ እንዳለበት ጠቋሚ ነው።

በባህር ዳር ከተማ በኩል ሁሉም የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በፋሲል ከነማ በኩል ያለውን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ዘንድ እጅግ ላቅ ያለ ትኩረት በሚሰጠው በዚህ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ ለአስር ያህል ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን በሰባት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ሲፈጽሙ ፋሲል ሁለት ጊዜ እንዲሁም ባህር ዳር ደግሞ አንድ ጊዜ ባለድል መሆን ሲችሉ በጨዋታዎቹ ዐፄዎቹ ስምንት ጎሎችን እንዲሁም የጣና ሞገዶቹ ደግሞ አራት ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ከድል መልስ ነገ የሚገናኙት በሁለት ነጥቦች እና በሦስት ደረጃዎች የሚበላለጡ የጦና ንቦቹ እና ቻምፒዮኖቹ የሚያደርጉት ጨዋታ በቡድኖቹ ባለው የነጥብ መቀራረብ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።

ከተከታታይ ሽንፈቶች መልስ መቐለ 70 እንደርታን በማሸነፍ ቀና ያለው ወላይታ ድቻ ነጥቡን ሃያ ስድስት አድርሶ የመጀመርያውን ዙር ለማገባደድ ተከታታይ ድሎች ካስመዘገበው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል።

ከኢትዮጵያ መድን እና አርባምንጭ ከተማ ጋር በጣምራ ከፍተኛው የግብ መጠን በማስቆጠር በ3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የጦና ንቦቹ በተቃራኒው ከፍተኛ የግብ መጠን በማስተናገድም በተመሳሳይ በ3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ቡድኑ በሁለት መርሐግብሮች አራት ግቦች ካስተናገደ በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ መረቡን ሳያስደፍር መውጣቱ እና ከዚህ ቀደም የነበረው ተጋላጭነት መቀነሱ በአወንታ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም አሁንም ችግሩን በዘላቂነት የመፍታት የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል። በነገው ጨዋታም የቀደመ የማጥቃት ጥንካሬው ያገኘ የሚመስለው እና በሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስቆጠረው ባንክ እንደመግጠማቸው ፈተናው ቀላል ይሆናል ተብሎ አይገመትም።

በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ ይዞ ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርበው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በነገው ጨዋታ ድል የሚያደርግ ከሆነ ዘለግ ላሉ ሳምንታት ከነበረበት የአደጋ ቀጠና የመራቅ ሰፊ ዕድል አለው።

ቻምፒዮኖቹ ከረዥም ጊዜ ጥበቃ በኋላ ጥሩ እንቅስቃሴያቸውን በውጤት ማጀብ ጀምረዋል። የአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ ቡድን ድሎችን ለማስመዝገብ ይቸገር እንጂ በአብዛኞቹ ጨዋታዎች ላይ የሚያስከፋ እንቅስቃሴ አላሳየም።
በቅርብ ሳምንታት ግን የቀደመ ጥንካሬው መልሶ ያገኘ የሚመስለው የቡድኑ የማጥቃት ጥምረት ቡድኑን ወደ ውጤት ጎዳና መልሶታል። ነገው ወሳኝ ፍልሚያም ከተጋጣሚው የመከላከል ድክመት አንፃር ይህንን አዎንታዊ ጎን በማስቀጠል ጨዋታውን በእጁ ለማስገባት እንደሚጥር ይገመታል።

በውድድር ዓመቱ በጣምራ አስራ አንድ ግቦች ያስቆጠሩት አዲስ ግደይ እና ኪቲካ ጅማ በጥሩ ወቅታዊ አቋም መገኘታቸውም ሀምራዊ ለባሾቹ  ተስፋ እንዲሰንቁ የሚያደርጋቸው እውነታ ነው።

በወላይታ ድቻ በኩል ናትናኤል አሲሮ አሁንም ከጉዳቱ ባለማገገሙ ለነገው ጨዋታ አይደርስም። ባለፈው ሳምንት ጨዋታ በሀዘን ምክንያት  ከቡድኑ ጋር ያልነበረው ያሬድ ደርዛ ግን ስብስቡን መቀላቀሉ ሲታወቅ የተቀሩት የቡድኑ አባላትም አባላት ለነገው ጨዋታ ተሟልተው የሚቀርቡ ይሆናል። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል አማካይ ፉዓድ ፈረጃ አሁንም ከጉዳቱ ባለማገገሙ  በነገው ጨዋታ አይሳተፍም። ለረጅም ሳምንታት በጉዳት ከቡድኑ ጋር ያልነበረው ሱሌማን ሀሚድ ወደ ልምምድ መመለሱ ለቡድኑ መልካም ዜና ቢሆንም ለነገው ጨዋታ የማይደርስ ሲሆን ሌሎች የቡድኑ አባለት ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አስር ጊዜ የግንኙነት ታሪክ ያላቸው ሲሆን ሁለቱም በተመሳሳይ በሦስት ጨዋታዎች ሲረቱ ቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተቋጭተዋል። ወላይታ ድቻ 10 ሲያስቆጥር ንግድ ባንክ በአንፃሩ 12 አስቆጥሯል።